ኢትዮጵያ በአልጄሪያ በተካሄደው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ውድድር 5 ሜዳልያዎችን አገኘች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያ በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፕዮና የተሳተፈው 5 ሜዳልያዎችን በማግኘት ውድድሩን አጠናቋል።

ውድድሩ ከአልጀርስ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ክሌፍ የተካሄደ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑ 2 ወርቅ፣ 1 ብርና 2 ነሀስ በጥቅሉ የ5 ሜዳልዎች ባለቤት ሆኗል።

አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች ውድድር በ19 ደቂቃ 44 ሴኮንድ በመግባት የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ሆናለች።

ፅጌ ገብረሰላማ በሁለተኛነት ስትገባ፥ ኬንያዊቷ ሄሌን ኢካላሌ ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በድብልቅ ሪሌ በሱ ሳዶ፣ ሞጎስ ጥዑማይ፣ ነጻነት ደስታና ቴሬሳ ቶሎሳ ተጣምረው በተሳተፉበት ውድድር 23 ደቂቃ ከ52 ሰከንድ በመግባት በ1ኛነት አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች አስር ኪሎ ሜትር ውድድር የሺ ካልአዩ ለኢትዮጵያ የነሀስ ሜዳልያ አስገኝታለች።

እንዲሁም በወጣት ወንዶች ስምንት ኪሎ ሜትር ሰሎሞን በሪሁን ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁን የኢትዮጲያ አትሌቲክስ ፌዴሬሺን አስታውቋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር እንደ አውሮፓውያን ዘመን ቀመር በ2011 በኬፕታውን መዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡