ወልዲያ ከተማ የ250 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትና ለአንድ አመት ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት ተወሰነበት

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ላይ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳለፈ።

የፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን ኮሚቴ ክለቡ ሚያዚያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ከፋሲል ከነማ ጋር አድርጎት በነበረው ጨዋታ ላይ የተፈጠረውን ድርጊት መነሻ በማድረግ የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቋል።

በዚህም ወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ 250 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍልና ቡድኑ ለአንድ አመት ያክል ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም ክለቡ የሚያደርጋቸውን ቀሪ የሜዳ ላይ ጨዋታዎች በፌዴሬሽኑ በተመዘገበና ከወልዲያ ከ500 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ በሚገኝ ሜዳ ላይ እንዲያደርግም ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በዕለቱ በጭማሪ ሰዓት ተቋርጦ የነበረው ጨዋታ ለፋሲል ከነማ ፎርፌ እንዲሰጥና ክለቡም በተፈጠረው ችግር የተጎዱ ዳኞችን የህክምና ወጪ እንዲሸፍንም ተወስኖበታል።

በተጨማሪም የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እና ተጫዋቹ ብሩክ ቃልቦሬ፥ እያንዳንዳቸው ለአንድ አመት ከስፖርታዊ ውድድሮች እገዳና የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

የተላለፈበትን የገንዘብ ቅጣትም ክለቡ ውሳኔው በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ እንዲከፍልም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘም ፌዴሬሽኑ በፕሪምየር ሊጉ 19ኛ ሳምንት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በተፈጠረው ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ሳቢያ በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ላይ የተለያዩ ቅጣቶችን አስተላልፏል።

ፌዴሬሽኑ ወላይታ ድቻ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ውሳኔ አስተላልፏል።

ከዚህ ባለፈም ክለቡ በቀጣይ በሜዳው ላይ የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች፥ ከሶዶ ቢያንስ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ እና በፌዴሬሽኑ በተመዘገበ ገለልተኛ ሜዳ እንዲያደርግ ወስኗል።