የስፔን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሪያል ማድሪድን ለማሰልጠን ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የስፔን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የለን ሎፔቴጉይ ከአለም ዋንጫው በኋላ ሪያል ማድሪድን ለማሰልጠን ተስማሙ።

ሎፔቴጉይ ስፔንን እየመሩ ወደ አለም ዋንጫው አምርተዋል።

በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከስፔን ጋር ከሚኖራቸው ቆይታ በኋላም ፈረንሳዊውን ዚነዲን ዚዳንን በመተካት ሪያል ማድሪድን ለማሰልጠን ተስማምተዋል።

አሰልጣኙ በነጮቹ ቤት ሶስት አመት ለመቆየት መስማማታቸውንም ክለቡ አስታውቋል።

የዚዳንን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ድል ማስቀጠልና የላሊጋውን ዋንጫ ወደ በርናባው መመለስ ቀጣዩ የቤት ስራቸው ይሆናል።

ሹመቱን ተከትሎም በሪያል ማድሪድ አዳዲስ ፊቶች ይኖራሉ እየተባለ ነው።

የእርሳቸውን ሹመት ተከትሎም የሮናልዶና ጋሬዝ ቤል የቆይታ ጉዳይ እንደገና ጥያቄ ተነስቶበታል።

ከዚህ ባለፈም ሪያል ማድሪድ ለረጅም ጊዜ ሲፈልገው የቆየው የማንቼስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴሂያ የዝውውር ጉዳይም እንደገና ይነሳል እየተባለ ነው።

አሰልጣኙ ከግብ ጠባቂው ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

ከአለም ዋንጫው ቀደም ብሎ ይፋ የተደረገው ሹመት ግን በስፔን ብሄራዊ ቡድን ውስጥ መከፋፈል እንዳይፈጥር ተሰግቷል።

ሎፔቴጉይ ስፔንን እየመሩ በ2018ቱ የአለም ዋንጫ ከሮናልዶዋ ፖርቹጋል ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና ደይሊ ሜይል