ፌደሬሽኑ ጅማ አባጅፋር ላይና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ

አዲስአበባ፣ ሰኔ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ጅማ አባጅፋር ክለብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጅማ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ በተፈተጸመ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ላይ ፌዴሬሽኑ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በውሳኔው የጅማ አባጅፋር ቡድን 150 ሺህ ብር እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን፥ እንዲሁም አንድ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ማለትም 200 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዲጫወት ተወስኖበታል፡፡

በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለፌዴሬሽኑ በሚያቀርበው የህክምና ማስረጃ መሰረት የጉዳት ካሳውን ጅማ አባጅፋር እንዲከፍል ተብሏል፡፡

የዲሲፕሊን ኮሚቴው አልቢትሩ ለጅማ አባጅፋር የቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሜዳ ገብተው ዳኛውን ለመደብደብ ሙከራ አደርገዋል በሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የ50 ሺህ ብር ቅጣት አስተላልፏል፡፡

እንዲሁም በጨዋታው ወቅት ስድስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች አምስት ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ በመመልከታቸው የዲሲፕሊን ኮሚቴው ቡድኑን 5 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ለደጋፊዎቻቸው ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲያስተምሩ እና የደጋናች ማህበር መሪዎች ተገናኝተው በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ከደጋፊዎች ጋር ውይይት እንዲያካሂዱ እንዲሁም ሰላም እንዲፈጠር ጥረት እንዲያደርጉ ይህንንም ለፌዴሬሽኑ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁ አዟል፡፡

በውድድሩ እለት በጨዋታ አመራሮች የተፈጸመ የስነስርዓት ጉድለት ወይም ስህተት ስለመኖሩ የብሄራዊ ሊግ ኮሚቴና የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ አጣርተው ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጡ ማስተላለፉንም ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አስፍሯል፡፡

ክለቦቹ የተወሰነባቸውን ቅጣት በ 10 ቀናት ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ የታዘዙ ሲሆን፥ ይህንን ተፈጻሚ የማያደርጉ ከሆነ ከውድድር እንዲታገዱና ከፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ምንም ዓይነት ትብብር እንዳያገኙ መወሰኑን ገልጿል፡፡