መንግስት ለድርቅ ተጎጂዎች የገዛው ተጨማሪ 200 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ጅቡቲ ወደብ ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2008 (ኤፍ. ቢ. ሲ) ኤል ኒኖ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ክስተት በኢትዮጵያ ባደረሰው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች አስፈላጊው የእህል ዕርዳታ በየነጥብ ጣቢያው የማድረሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እስካሁን ከተሰራጨው እህል በተጨማሪ መንግስት ለተጎጂዎች የሚውል 600 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ለመግዛት አዟል።

ከዚህም ውስጥ 200 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን ነው ያመለከቱት።

ወደብ የደረሰውን የእርዳታ እህል በፍጥነት ወደ ሃገር ውስጥ አስገብቶ ወደ ተረጂዎች መንደር ለማድረስ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች እየተመቻቹ መሆኑን አስታውቀዋል።

ስርጭቱን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ይረዳ ዘንድ በሃገሪቱ ያሉ የእርዳታ እህል የሚደርስባቸው የነጥብ ጣቢያዎች ተለይተው ያንን የሚመራና የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል ያሉት አቶ ደመቀ፥ በዚህ አብይ ኮሚቴ ውስጥ የእርዳታ እህሉ ቅድሚያ የትራንስፖርት አገልግሎት አግኝቶ በተቀላጠፈ መልኩ እንዲሰራጭ የሚሰራ አካል በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የተዘረጋው የባቡር መስመር የእርዳታ እህሉን ከጅቡቲ እስከ አዳማ እንደሚያጓጉዝና አገልግሎቱን በቶሎ ለማስጀመር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በድርቁ የተነሳ የሰው ህይወት አልፏል እያሉ እያሰራጩ ካለው ዘገባ አንጻር በተጨባጭ ያለው እውነታ ምን ይመስላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፥ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ከተለያዩ አካላት ጋር እንደሚሰሩ ይታወቃል ከዚያ በላይ ግን አፍ ለማዘጋት አልያም ለማስተባበልና ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን ረሃብ የሚባለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ብለዋል።

"ዕርዳታ ባለመድረሱ ሰው ተሰዶ የሄደበት ዕርዳታ ባለመድረሱ ርሃብ የተከሰተበት ሁኔታ የለም፤ በየትኛውም ጊዜ በማንኛውም መንገድ በህይወት ያለ ሰው ሕይወቱ ሊያልፍ ይችላል" ያሉት አቶ ደመቀ፥ "ዋናው ጥያቄ ህልፈቱ የተከሰተው በረሃብ የመጣ ነው ወይ የሚለውን ህዝቡ ውስጥ ገብቶ ማየት ሚዛን ይደፋል የሚለው አሳማኝ ይሆናል" ብለዋል።