በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ያሳወቀ አካል እንደሌለ የክልሉ መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 28፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በይፋ ለክልሉ መንግስት ያሳወቀ አካል እንደሌለ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር ገለጹ።

አቶ ሙክታር፥ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ሀሳባቸውን የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብት ያላቸው መሆኑን በመናገር፥ በአሁኑ ሰዓት ግን በሰላማዊ ሰልፍ ስም እየተላለፈ ያለው ጥሪ እውቅና የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች እየተላለፈ ያለው ጥሪን አስመልክቶ ማንኛውም ህጋዊ ቁመና ያለው አካል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ይችላል፤ ሆኖም ግን ህጋዊ የሆነ አካል ሰልፉን በባለቤትነት በሙሉ ሃላፊነት መውሰድ እና አስፈላጊውን ነገሮች ማሟላት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ማንኛውም ህጋዊ የሆነ አካል ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በሚያስብበት ጊዜ ሰልፉን የሚያካሂድበት ስፍራ እና መቼ እንደሚያካሂድ ሀላፊነቱን በመውሰድ በህጉ መሠረት ማሳወቅና መጠየቅ እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ሆኖም ግን ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች በሰላማዊ ሰልፍ ስም እየተላለፈ ያለው ጥሪ እውቅና የሌለውና በሰላማዊ ሰልፍ ስም ለብጥብጥ የተጠራ መሆኑን አቶ ሙክታር ተናግረዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ እስካሁን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አንድም ህጋዊ ጥያቄ አለመቅረቡንና ሰልፉን በባለቤትነት አካሂዳለው የሚል አካል አለመኖሩን በምክንያትነት ያነሳሉ።

እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ስም እየተላለፉ በሚገኙ ጥሪዎች ላይ ህብረተሰቡ እንደ ጠብመንጃ ያሉ የጦር መሳሪያዎችን ይዞ እንዲወጣ የሚያነሳሱ አካላት መኖራቸው እና በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ጥሪ እያስተላለፉ የሚገኙ አካላት ከዚህ በፊት የክልሉ ሰላም እንዲደፈርስ እና የሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት የነበሩ ናቸው ብለዋል።

ስለዚህም ይላሉ ርዕስ መስተዳድሩ፥ በሰላማዊ ሰልፍ ስም የሚደረገው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ሀገርንም ሕዝብንም የሚጎዳ በመሆኑ ሕብረተሰቡ በጥፋት ኃይሎች ከዚህ ቀደም የደረሰበትን ጉዳት ተገንዝቦ በድርጊቱ ላይ ባለመሳተፍ የጥፋት ሴራው ዳግም በኦሮሚያ መከሰት የለበትም ብሎ መቃወም አለበት ብለዋል።

ህብረተሰቡ ህጋዊ እውቅና ባላገኘ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዳይሳተፍም አቶ ሙክታር አሳስበዋል።

በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በ2008 በጀት ዓመት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን አቶ ሙክታ ከድር በመግለጫቸው ላይ አብራርተዋል።

በክልሉ በመንገድ ልማት፣ በጤናና በትምህርት ዘርፍ በበጀት ዓመቱ የተሰሩት ሥራዎች በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ሲታዩ አፈፃፀማቸው አበረታች ቢሆንም በቀጣይ በየዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በተከሰተው ድርቅ የክልሉ መንግስት ትልቅ በጀት መድቦ አስቀድሞ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ርእሰ መስተዳድሩ፥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰራው ሰፊ ስራ የዜጎችን ህይወት መታደግ መቻሉን ገልፀዋል።

ድርቁን በዘላቂነት ለመቅረፍም አርሶ አደሩ ያለውን የውኃ ኃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከክረምቱ ወራት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በክልሉ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስም የተሰሩት ስራዎች ጥሩ ጅማሮ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

በቀጣይም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስም የክልሉ መንግስት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ በማውጣት እየሰራ እንደሚገኝ አመለክተዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራን በመተመለከተ የክልሉ መንግስት ልዩ ዕቅድ አውጥቶ በአጭር ጊዜያት ውስጥ በሰራው ሥራ ከ500 ሺህ በላይ ወጣቶች በመረጡት የሥራ መስክ ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

ተመሳሳይ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የኦሮሚያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት ዘግቧል።