መንግስት ህግ የማስከበር ሀላፊነቱን ለመወጣት ህገወጥ ድርጊቶችን የመግታት ስራ ይሰራል - ጠ/ሚ ሃይለማርያም

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 29 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገወጥ ድርጊቶችን ለመግታት መንግስት ህግን ለማስከበር እንደሚገደድና ሃላፊነቱን እንደሚወጣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊና የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም መላ ህዝቡ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ እና በሰለጠነ አግባብ መፍታት የሚችልበት ሰፊ እድል እንዳለው ገልፀው፥ ባለቤቱ በማይታወቅ እና በማህበራዊ ድረ ገጽ ከሚመራ ህገ ወጥ ሰልፍ ጥሪ ራሱን እንዲቆጥብ አሳስበዋል።

ሰሞኑን በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተካሄዱ እና እየተጠሩ ያሉ ሰልፎች አግባብነት እንደሌላቸው አንስተዋል።

በህገ መንግስቱ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት የተጠበቀ ቢሆንም፥ ሰሞኑን የተካሄዱት እና ለማካሄድ የሚፈለጉት ሰልፎች ግን ከህግ አግባብ ውጪ ባለቤት የሌላቸውና በማህበራዊ ድረ ገጾች የተጠሩ ያልተገቡ ቅስቀሳዎች ናቸው ብለዋል።

በነዚህ ሰልፎች ከህዝቡ ጥያቄ ባፈነገጠ እና ህብረተሰቡን የማይወክሉ የጸረ ሰላም ሀይሎች አቋም ሲንጸባረቅ በአደባበይ ተስተውሏል ነው ያሉት።

የተንጸባረቁት አቋሞች እና መፈክሮች የኦሮሞንም ሆነ የጎንደርን ህዝብ የሚወክሉ አለመሆናቸውን መንግስት ይገነዘባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

እነዚህ ህዝቦች አስከፊውን ስርዓት ለመናድ የተጋደሉ እና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመሆን አሁን እያደገች ለመጣችው ኢትዮጵያ ሚናቸው የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህ ስርዓትም የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ በቋንቋው የመጠቀም እና ባህሉን የማሳደግ ጉልህ ነጻነቱን የተጎናጸፈበት በመሆኑ፥ መላ ህዝቡ ህገ መንግስቱን ሲጠብቀው እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

አቶ ሃይለማርያም በመግለጫቸው እንዳሉት፥ መንግስት ቀደም ብሎ ከህዝቡ ጋር ባካሄደው ውይይት እና በራሱ ግምገማም በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን በመቀበል ለመፍትሄው እየሰራ ነው።

አሁንም ያልተመለሱ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን መንግስት ይረዳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እነዚህን ጉዳዮች ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት ርብርብ እንደሚደረግም ነው የገለጹት።

መንግስት ህግ ለማስከበር ህገወጥ ድርጊቶችን የመግታት ሀላፊነቱን ይወጣልም ብለዋል።

በመግለጫቸው የህዝቡን ትክክለኛ ጥያቄ ተከትሎ በተሳሳተ መንገድ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ከሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ህብረተሰቡ ራሱን መጠበቅ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በቀጣይም ገዥው ፓርቲ እንድ ድርጅት ለተሃድሶ መስመሩ እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

በዚህ የግምገማ መርሃ ግብር ኢህአዴግ ያስቀመጠው የተሃድሶ የመስመር ጥራት ውጤታማነት ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ብለዋል።

ይህም በመንግስት እና በድርጀቱ ያሉ ጉድለቶችን በማጥራት እና ግልጽ ውይይት ከመላው ህዝብ ጋር በማድረግ በአዲሱ አመት የልማት ግቡን ለማሳካት ርብርብ የሚደረግበት አመት እንደሚሆንም ገልፀዋል።

 

በኤልያስ ተክለወልድ