በድርቅ በተጠቁ ክልሎች የሰውና የእንስሳት ህይዎትን ለመታደግ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 25 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሶስት ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ህይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ከኤል ኒኖ ክስተት በኋላ የመጣው የላ ኒና ክስተት፥ አምና በጎርፍ የመታቸው የደቡብ፣ ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ዘንድሮ በድርቅ ተጠቅተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ እንደሚሉት፥ አሁን ላይ ዘጠኝ የክልሉ ዞኖች በድርቅ ተመተዋል፤ ከዚህ ውስጥ ችግሩ በሶስቱ የከፋ መሆኑን በመጥቀስ።

በኦሮሚያ ክልልም ድርቁ በቦረና፣ በባሌ ቆላማ ስፍራዎች፣ በጉጂ እና ምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች መከሰቱን የክልሉ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ስለሺ ጌታሁን ተናግረዋል።

በደቡብ ክልልም ከመስከረም አጋማሽ እስከ ህዳር ወር መጨረሻ መዝነብ የነበረበት ዝናብ ያልተስተካከለ በመሆኑ፥ በሰገን አካባቢ፣ ጋሞ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ድርቅ ተከስቷል።

በድርቁ ሳቢያም የአርብቶ አደሩ ሁለንተና የሆኑት የቁም እንሳስት ለችግር ተጋልጠዋል።

በሶማሌ ክልል በጎች፣ ከብት እና ግመሎች በድርቁ ሳቢያ ሲሞቱ፥ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልልም በእንስሳት ህይወት ላይ ጉዳት ደርሷል።


ድርቁ በሰው ህይዎት ላይ ጉዳት ባያደርስም፥ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታን ለእንስሳቱም መኖ እና ውሃ እያቀረቡ መሆኑን ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ብለዋል።

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፥ በሶማሌ ክልል 10 ሺህ ኩንታል አልሚ ምግብ፣ 500 ኩንታል የስንዴ ዱቄት እና 50 ሺህ እስር ሳር ለእንስሳት መኖነት ቀርቦ ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎችየ፥ በ60 ሚሊየን ብር ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፥ የሶማሌ ክልልም 300 ሚሊየን ብር መድቦ ምላሽ እየሰጠ ነው።

የደቡብ ክልል እንስሳቱን ከፓርኮች መኖ ሰብስቦ በማምጣት ከፌደራል መንግስት ከተሰጠው መኖ ጋር ቀላቅሎ ለእንስሳቱ እያቀረበ እንደሚገኝ የሚገልጹት ደግሞ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ ናቸው።

የእንስሳቱን ሁኔታ መታደግ ግን ቀጣዩ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነባቸውም ርዕሳነ መስተዳድሮቹ አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የቦረና ቁም እንስሳት ዝርያን መታደግ፣ ሶማሌ ክልል እንስሳቱን በግዢ ከሞት ማስጣልን ታሳቢ አድርገው እየሰሩ ነው።

የደቡብ ክልል ደግሞ ውሃ ገብ በሆኑ አካባቢዎች በ45 ቀናት ውስጥ የሚደርሱ የእንስሳት መኖዎችን ማልማትን ታሳቢ አድርጎ እየሰራ መሆኑም ተጠቅሷል።

በሶስቱ ክልሎች የተወሰኑ ስፍራዎች የተከሰተው ድርቅ ህጻናትን ከትምህርት ገበታ አርቋቸዋል፤ በኦሮሚያ ቦረና እና ጉጂ ዞን ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል በደቡብ እና ሶማሌ ክልልም እንደዛው።

ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንድ ሚሊየን ህፃናት የትምህርት ቤት ወንበሮች ባዶ ሆነው ታይተዋል።

ክልሎቹ የትምህርት ቤት ምገባ በመጀመር ተማሪዎቹን ለመመለስ እየሰሩ መሆኑን ሲጠቅሱ፥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የትምህርት መርሃ ግብሩን በመከለስም ቢሆን መመለስ ይገባል ብለዋል።

ዋና ችግራችን ውሃ አቅርቦት ነው የሚሉት ሶስቱ ክልሎች፥ ውሃ ለማቅረብ የሚያስችል ተሽከርካሪ እጥረትን በችግርነት አንስተዋል።

የውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፤ በፌደራል መንግስት ደረጃ ሊሆን የሚገባውን ድጋፍ እናቀርባለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የክልሎቹ መንግስታት እስካሁን ለድርቁ የሰጡትን ምላሽ ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፌደራል መንግስቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ህይወት መታደግን ቅድሚያ ሰጥተው ለሚሰሩት ክልሎች ከዕለት ደራሽ አቅርቦት እስከ በጀት ድጋፍ የደረሰ እርዳታ እንደሚያደርግ በመጥቀስ።

 

 

 

በዳዊት መስፍን