የሳምሰንግ ምክትል ፕሬዚዳንት በሙስና ወንጀል ሊመረመሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የደቡብ ኮሪያ ልዩ የምርመራ ቢሮ እንደገለጸው የሳምሰንግ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ሊ ጄ-ዮንግ ከፖለቲካዊ ሙስና ጋር በተያያዘ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው።

ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ የፓርክ ጊዮን ሀይ አብሮ አደግ እና ወዳጅ በሆኑት ቾይ ሱን-ሲል ለተቋቀቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅት የ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር እርዳታ አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ሳምሰንግ ይህን ድጋፉን ያልተገባ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት አስቦ አድርጎታል በሚል ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተይዘው ልዩ ምርመራ እንዲደረግባቸው ቢሮው አዟል፡፡

በመሆኑም ሚስተር ሊ በነገው ዕለት ልዩ ምርመራ እንደሚደረግባቸው ነው የተነገረው።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱ ፓርላማ ባለፈው ታህሳስ ወር ባደረገው ስብሰባ ላይ ቀርበው ሳምሰንግ ለሁለት ድርጅቶች ከ17 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ቢያምኑም፥ ያልተገባ ጥቅምን ለመፍጠር አይደለም የሚል ማስተባበያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህ ሳምንት ቀደም ብሎ ሁለት የኩባንያው ሃላፊዎች በልዩ መርማሪዎች ተጠይቀው ቃል የሰጡ ሲሆን፥ ከወንጀለኛነት ይልቅ ለምስክርነት እንዲቆሙ ተደርገዋል፡፡

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ