ከቡና ንግድ ከ75 ሚሊየን ዶላር በላይ በማሳጣት የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ56 ነጋዴዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር መንግስትን ከ75 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል በሚል የተጠረጠሩ የቀድሞ የቡና እና ሻይ ገበያ የቡና ገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተርና የቡድን መሪ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የፌዴራል ፖሊስ የፋይናንስ ወንጀሎች ምርመራ ተጠርጣሪዎቹ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት በማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል።

ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ጌታሁን ቢኮራ እና ታጠቅ ግርማ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

በንግድ ሚኒስቴር የቡና እና ሻይ ገበያ ከ2000 እስከ 2007 ዓ.ም በስራ ሃላፊነት ተመድበው ሲሰሩም መንግስት የሰጣቸውን ስልጣንና ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከነጋዴዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከ56 በላይ ቡና ነጋዴ ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡና ገዝተው በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ በኩል ወደ ውጭ ሃገር እንዲላክ ቁጥጥር ማድረግ ሲገባቸው አለማድረጋቸውን ነው ፖሊስ የገለፀው።

በዚህም ሃገሪቱ ከ56 ነጋዴዎች በላይ ለሰባት ዓመታት ቡናውን ወደ ውጭ ቢልኩ ኖሮ ይገኝ የነበረውን ከ75 ሚሊየን 686 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል በሚል ተጠርጥረው የፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሰር አውሏቸዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የወንጀል ችሎት በማቅረብም ምርምራውን በሰውና በሰነድ ማስረጃ በስፋት ለማጣራት ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ የተጠረጠርንበት ጉዳይ ቀድሞ ክፍተቱ እንዳለ በማጥናት 56 ነጋዴዎች በትክክል የተቀበሉት ቡና ወደ ውጭ እንደማይልኩ ለይተን ያዘጋጀነውና ማስተካከያ እንዲወሰድ የጠየቅነው እኛ ነን፤ ክፍተቱን አጥንተን መፍትሄውን ማዘጋጀታችን አያስጠረጥረንም ብለዋል ለፍርድ ቤቱ።

ፖሊስ የስራ ሃላፊዎቹ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸውና ከነጋዴዎች ጋር በነበራቸው መመሳጠር የተፈጠረ በመሆኑ የኦዲት ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን እየለየ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲጠይቁ ፖሊስ የጀመርኩትን ምርመራ መረጃ በመደበቅ ያደናቅፉበኛል፤ ሌሎች ተጠርጣሪዎች መረጃ እንዲያሸሹ ያደርጋል በማለት የዋስትና መብት እንዳይፈቀድ ጠይቋል።

የግራና ቀኙ ክርክር ያደመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ ተጨማሪ የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

  

 

በበላይ ተስፋዬ

android_ads__.jpg