ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ወታደር እንደማትቀበል ገለጸች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በሃገሯ እንደማታሰፍር ገለጸች።

ባለፈው ነሃሴ ወር የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሃገሪቱ ተጨማሪ 4 ሺህ የሰላም አስከባሪ ወታደር መስፈር እንዳለበት ገልጾ ነበር።

መንግስት በበኩሉ አሁን ላይ በሃሪቱ ሰላምና መረጋጋት በመስፈኑ ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ ሃይል ማስፈሩ አላስፈላጊ ነው ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ማዌይን አሪክ፥ መንግስት ያለ ሰላም አስከባሪ ጣልቃ ገብነት የሃገሪቱን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት የማረጋገጥ ብቃት አለው ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ኩኦል ማንያንግ በበኩላቸው፥ ሃገራቸው ምንም አይነት የሰላም አስከባሪ ሃይል አያስፈልጋትም ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሃገሪቱ ርቀው ያሉ አካላት ደቡብ ሱዳን፥ ጦርነት ላይ እንደሆነች ማሰባቸው ስህተት ነው።

የሳልቫ ኪር አስተዳደር ባለፈው ህዳር ወር ሰላም አስከባሪ ሃይሉ በሃገሪቱ እንዲሰፍን ይሁንታን ሰጥቶ ነበር።

የአሁኑ ውሳኔም የህዳር ወሩን ውሳኔ የቀለበሰ ሆኗል።

በሳልቫ ኪር እና በቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር፥ በ2013 ወደ ጦርነት ያመራው የፖለቲካ ልዩነት በ10 ሺህዎች ለሚቆጠሩ የሃገሬው ዜጎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው ሃምሌ ወር ዳግም ያገረሸው ግጭት ሪክ ማቻርን ለስደት ዳርጓል።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ የኪር አስተዳደር ዘርን መሰረት ያደረግ ጥቃት ይፈጽማል በማለት ይወነጅላል።

ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊ ሃገር ከሆነችበት የፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በሃገሪቱ ከ13 ሺህ በላይ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ይገኛሉ፡፡

 

 

 

ምንጭ፦ አልጀዚራ