የአፍሪካ ህብረትን ለመምራት የቀረቡት ዕጩዎች እነማን ናቸው?

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ህብረት ከተመሰረተ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ ይዟል።

ከ54 ዓመት በፊት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስም የተመሰረተው የአፍሪካውያን ስብስብ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2001 ጀምሮ ወደ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽንነት ተሸጋግሯል።

ወደ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽንነት ከተሸጋገረ በኋላ ዶክተር ንኮሶዛና ድላሚኒ ዙማን ጨምሮ አራት ሊቀነመናብርት ተፈራርቀውበታል።

አማራ ኤሲ፣ አልፋ ኦማር ኮናሬ፣ ዣን ፒንግና ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ደግሞ ኅብረቱን በሊቀመንበርነት የመሩ ናቸው።

ህብረቱ ባለፈው ሐምሌ በሩዋንዳ ኪጋሊ ባካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ሊቀመንበሩን የመምረጥ ጥረቱ ዕጩዎች በአባል አገራት ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ባለማግኘታቸው ለማራዘም ተገዷል።

እናም አሁን በአዲስ አበባ በሚደረገው 28ኛው የመሪዎች ጉባዔ በዳግመ ምርጫ ኅብረቱን በሊቀመንበርነት የሚመራ ሰው ይመረጣል።
ህብረቱን ለመምራት በዕጩነት የቀረቡት እነማን ናቸው?

አሚና መሐመድ

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አሚና መሐመድ ለሊቀመንበርነት ሰፊ ግምት የተሰጣቸው ዕጩ ናቸው።

ከሶማሌ ጎሳ የተወለዱት ኬንያዊቷ ዶክተር አሚና የሕግ ባለሙያ፣ ዲፕሎማትና የፖለቲካ ሰው ሲሆኑ ኬንያን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

የ55 ዓመቷ ዶክተር አሚና የዓለም ዓቀፍ የስደት ድርጅት ሊቀመንበርና የዓለም ንግድ ድርጅት ምክር ቤት አባል እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ መርሃ ግብር ረዳት ጸሃፊና ምክትል ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል።

ሶማሊኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ስዋሂሊና ሩስኪን እንዲሁም ፈረንሳይኛን የሚናገሩት አሚና በጄኔቫ ስዊዘርላንድ የኬንያ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

አሁን ድረስም የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ዶክተር አሚና የምሥራቅ አፍሪካ ህብረተሰብ ድጋፍ ያገኙ ቢሆንም ለማሸነፍ በምርጫው ጠንካራ ተሳትፎ ያላቸው የፈረንሣይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት ድጋፍን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።

ፔሎኖሚ ቬንሰን-ሞታይ

የቀድሞ ጋዜጠኛ ቦትስዋናዊቷ ፔሎኖሚ ቬንሰን-ሞታይ ሌላኛዋ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

ፔሎኖሚ የቦትስዋና ገዢ ፓርቲ ለሆነው ለዴሞክራሲዊ ፓርቲ የፖለቲካ ተወካይ ሆነው ረዘም ላለ ጊዜ አገልግለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር እስከ 2014 ድረስ የቦትስዋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆንም ሰርተዋል።

ፔሎኖሚ እ.አ.አ ከ2001 እስከ 2002 የቦትስዋና የሥራ፣ የትራንስፖርትና የኮሚዩኑኬሽን ሚኒስትር፣ ከ 2002 እስከ 2004 የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የዱር አራዊትና የቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

በተጨማሪም በ2009 የኮሚዩኒኬሽን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር በኋላ ላይም የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

ፔሎኖሚ ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት ሰፊ ድጋፍ ያላቸው ቢሆንም ከሌሎች ተፎካካሪዎች ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው እየተነገረ ነው።

ሙሳ ፋቂ መሃማት

ሌላኛው ዕጩ የቻድ ዜጋ የሆኑት ሙሳ ፋቂ መሃማት ናቸው።

ሙሳ መሃማት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ 2003 እስከ 2005 የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ማገልግል ችለዋል።

ፖለቲካኛው ሙሳ ከ 2007 እስከ 2008 ባለው ጊዜም የአገሪቷ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል።

በዛው ዓመት የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ግለ ታሪካቸው ያሳያል።

ሙሳ የአገሪቷን ሁለት ተቋማት በሚኒስትርነት የመሩና የቻድ የስኳር ኩባኒያንም በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸው ታውቋል።

የፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ካቢኔ ዳይሬክተርና የ2001 ምርጫ ዘመቻ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።

እናም በምርጫው የፈረንሣይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት ድጋፍ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

አጋፒቶ ምባ ሞኩይ

የኢኳቶሪያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አጋፒቶ ምባ ሞኩይ ሌላኛው የህብረቱ ዕጩ ናቸው።

አጋፒቶ በሥራቸው የፓን አፍሪካኒዝም ሃሳብን የሚያቀነቅኑና ራሷን የቻለችና የበለጸገች አፍሪካን ለመግንባት የሚተጉ ዲፕሎማት እንደሆኑ ይነገራል።

አጋፒቶ በሚኒስትርነታቸው ኢኳቶሪያል ጊኒ በአፍሪካና በዓለም ዘንድ የፖለቲካ ተሰሚነቷ ከፍ እንዲል ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ይነሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው አስቀድሞ የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት የዓለም ዓቀፍ ጉዳይ ዋና አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።

ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የኢኳቶሪያል ጊኒ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

ለ18 ዓመታት ገደማ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ውስጥም የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል።

አብዱላዪ ባዚልይ

ሴኔጋላዊው ዶክተር አብዱላዪ ባዚልይ ፖለቲከኛና ዲፕሎማት ናቸው።

ህብረቱን በሊቀመንበርነት ለመምራት ዕጩ የሆኑት ዶክተር አብዱላዪ የሴኔጋል የፖለቲካ ፓርቲ ለሆነው የዴሞክራቲክ ሊግ ዋና ጸሃፊ ሆነው አገልግለዋል።

ዶክተር አብዱላዪ የሴኔጋል የአካባቢና የኢነርጂ ሚኒስትር እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የመካከለኛው አፍሪካ ልዩ ተወካይ ሆነው ሰርተዋል።

እናም ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን በሊቀመንበርነት "ማን ይምራው" የሚለውን በዚህ ሣምንት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ