በደቡብ ሱዳን የመንገደኞች አውሮፕላን ተከሰከሰ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመንገደኞች አውሮፕላን በደቡብ ሱዳን ዋኡ አውሮፕላን ማረፊያ መከስከሱ ተሰምቷል።

አውሮፕላኑ 44 መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር ነው የተነገረው።

የአውሮፕላን መከስከስ አደጋው እንደተሰማ አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ሳይሞቱ አይቀርም የሚሉ መረጃ ወጥተዋል።

የሳውዝ ሰፕረም አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ ግን በአደጋው ምንም አይነት የሰው ህይወት አልጠፋም ብለዋል።

አውሮፕላኑ መከስከሱን ተከትሎ በእሳት ከመያያዙ በፊት ሁሉንም ተሳፋሪዎች ማውጣት መቻሉንም ለናሽናል ኮሪየር ተናግረዋል።

የሀገሪቱ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ቦና ጋውዴንሲዮ 14 ተሳፋሪዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ማለታቸውን ሜትሮ አስነብቧል።

በጁባ የሚገኝ አይ የተሰኘ የሬዲዮ ጣቢያም አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘጠኝ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ዘግቧል።

ለሬውተርስ አስተያየት የሰጡ የአደጋ ጊዜ ሰራተኛ በበኩላቸው "አንድም የአውሮፕላኑ ተሳፋሪ አልሞተም፤ በርካቶቹ ግን ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።

የሳውዝ ሰፕረም አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከጁባ ተነስቶ ዋኡ አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፍ ሲሞክር ነው የመከስከስ አደጋው ያጋጠመው።

 

 

ምንጭ፦ ሲጂቲኤን አፍሪካ፣ ሜትሮ እና ኢንዲፐንደንት