ኤፍ ቢ አይ ሩስያ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ስለመግባቷ ለማረጋገጥ ምርመራ እያደረግኩ ነው አለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች በሚል የሚቀርበውን ውንጀላ እየመረመረ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አደረገ።

የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚ እንደገለጹት፥ ከዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ከሩስያ መንግስት ጋር ሊኖራቸው የሚችለው ትስስርም እየተጣራ ነው።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ እና ሩስያ ግንኙነት ነበራቸው ወይንስ የላቸውም የሚለውን ለማወቅም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኤፍ ቢ አይ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ወንጀል ስለመፈጸሙም እያጣራ ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በበኩላቸው የምርጫው ውጤት ከሩስያ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም ሲሉ በተደጋጋሚ ገልፀዋል።

ሩስያም በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ምንም አይነት ሙከራ አለማድረጓን ስትገልፅ ቆይታለች።

የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ግን ጉዳዩ ምንም እንኳን ውስብስብ ቢሆንም ትክክለኛ መረጃዎችን እስክናገኝ ድረስ የምርመራ ስራው ይቀጥላል ብለዋል።

በሌላ በኩል ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልኬን ጠልፈው ይሰሙ ነበር በሚል ያቀረቡት ወቀሳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጀምስ ኮሚ ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ