ፓርቲዎች በቀጣይ ለሚያካሂዱት ውይይትና ድርድር ሶስት አባላት ያሉት አደራዳሪ መረጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ ለሚያካሂዱት ውይይት እና ድርድር ከመካከላቸው በቋሚነት የሚያደራድራቸው ሶስት አባላት ያሉት አደራዳሪ መርጠዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ ባካሄዱት ዘጠነኛ ዙር ስብሰባ ላይ አደራዳሪዎቹን የመረጡ ሲሆን፥ አደራዳሪው ሶስት አሊያም አምስት አባላትን ያቀፈ ይሁን የሚል ሀሳብን በአማራጭነት አቅርበው ነበር።

በአደራዳሪዎቹ ቁጥር ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላም ሶስት አደራዳሪዎች እንዲሆኑ በመስማማት በእጩነት ከቀረቡላቸው አምስት ሰዎች ሶስቱን ለአደራዳሪነት መርጠዋል።

በዚህም መሰረት አቶ አሰፋ ሀብተወለድ ከመኢአድ የአደራዳሪው ሰብሳቢ፣ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ከኢዴፓ የአደራዳሪው ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ አለማየሁ ደነቀ ከአትፓ የአደራዳሪው ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።

በአደራዳሪነት የተመረጡት ግለሰቦች በድርድሩ ሂደት የአደራዳሪነት ሚና ብቻ ሚጫወቱ ሲሆን፥ የፖቲካ ፓርቲያቸውን በመወከል በተደራዳሪነት የማይቀርቡ መሆኑም ተገልጿል።

በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአጀንዳ አደራጅ እና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴም በዛሬው ስብሰባቸው መርጠዋል።

በምርጫው ወቅትም ፓርቲዎቹ እህአዴግ ድርድሩን የጠራ በመሆኑ በአጀንዳ አደራጅ እና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፍ ተስማምተዋል።

ቀሪ ሁለት የኮሚቴው አባላትን ለመምረጥም አራት እጩዎች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱን በድምፅ ብልጫ መርጠዋል።

በዚህም መሰረት አቶ ገብሩ ብርኸ ከኢፍዴኃግ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ፥ አቶ አስመላሽ ገብረስላሴ ከኢህአዴግ እንዲሁም አቶ መላኩ መሰለ ከኢራፓ የኮሚቴው አባላት ሆነው ተመርጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ በዛሬው ውይይታቸው ሶስት አጀንዳዎች ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ በ8ኛው ዙር የተደረገ ውይይት ቃለ ጉባኤም አፅድቀዋል።

በ8ኛው ዙር ያፀደቁትን ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ደንብ ላይም ያቀረቧቸው ማሻሻያዎችና ሀሳቦች መካተታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፥ በደንቡ ውስጥ ያልተካተቱ እና መውጣት ያለባቸው ሀሳቦች ላይ እርምት በማድረግ ደንቡን አፅድቀዋል።

ፓርቲዎቹ በድርድር ደንቡ መሰረት ከነገ ጀምሮ በ15 ቀናት ውስጥ የመደራደሪያ አጀንዳዎቻቸውን የአጀንዳ አደራጅ እና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ እንደሚያስገቡም ታውቋል።

ከ15 ቀን በኋላም አደራዳሪ ኮሚቴዎቹ ቀን በመወሰንና ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥሪ በማድረግ ስራቸውን እንደሚጀምሩም ተገልጿል።


በበላይ ተሰፋዬ