ግብጽ እና አሜሪካ ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ከአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ጄምስ ማቲስ ጋር በወታደራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በካይሮ መክረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ጋር በነበራቸው ውይይትም በሁለቱ ሀገራት በስትራቴጂያዊ አጋርነት ላይ በትኩርት መምከራቸውን የግብጽ ፕሬዚዳታዊ ቃል አቀባይ አላ ዮሱፍ ተናግረዋል፡፡

ኤል ሲሲ እና ማቲስ የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና በፀረ ሽብር ተግባራት ላይ በጋራ ለመስራት ነው የመከሩት፡፡

ግብጽ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የሽብር ቡድኖችን ለማዳከምና ለማስወገድ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ እንዳይደረግላቸው እና ድጋፍ በሚያደርጉ ሀገራት ላይ ገደብ እንዲጣል ካይሮ ከዋሽንግተን ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት ተብሏል፡፡

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ጄምስ ማቲስ በበኩላቸው ዋሽንግተን ከግብጽ ጋር መከላከያ ኃይል ዘርፍ በጋራ እንደመትሰራ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከሳዑዲ ዓረቢያ ተነስተው ካይሮ የገቡት እስራኤል፣ ኳታር እና ጂቡቲን ጨምሮ ግብጽም የጉብኝታ አካል በመሆኗ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም የመከላከያ ማቲስ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት በካይሮ እያደረጉ ሲሆን፥ አሜሪካ ከሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ልዩ እና ስትራቴጂዊ ግንኙነትና ትብብሮሽ ለማጠናከር የሚያስችል ወይይትን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማቲስ ዛሬ ወደ እስራኤል የሚያመሩ ሲሆን ነገ ደግሞ ኳታርን ይጎበኛሉ፡፡

 

በፈረንጆቹ ሚያዚያ 23 በጂቡቲ ከፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ ጋር ከተገናኙ በኋላ የቀጣናው ሀገራት ጉብኝታቸውን እንደሚያጠናቅቁ ነው የተጠቆመው፡፡

 

 

 

 

ምንጭ፡- አህራም ኦንላይን እና ሲጂቲኤን አፍሪካ