ኢትዮጵያ በ6 ወራት ብቻ 256 ታላላቅ የሳይበር ጥቃቶች ደርሰውባታል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ኢትዮጵያ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 256 ታላላቅ የሳይበር ጥቃቶችን አስተናግዳለች።

ጥቃቱ በቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ በፋይናንስ ተቋማት እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ያነጣጠረ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ መሃመድ እድሪስ፥ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ እንደሚጎበኟት ተናግረዋል።

የሳይበር ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊው፥ ሰሞኑን 155 ሀገራትን ያጠቃው “ወነክራይ” የተባለው የሳይበር ጥቃት ካነጣጠራቸው 11 የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

የጥቃቱ ኢላማዎች ደግሞ የህክምና፣ የትራንስፖርት፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ታላላቅ የመሰረተ ልማት አውታሮች መሆናቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው ነው ያነሱት።

አንደ አቶ መሃመድ እድሪስ ገለጻ፥ የግለሰቦች መገልገያ ኮምፒውተሮችም የመሰል ጥቃቶች ሰለባዎች ናቸው።

የጥቃቶቹ ባህሪ ተለዋዋጭነት እና ጉዳት ማድረስ አቅማቸው መለያየት በዘርፉ ያለውን ቴክኖሎጂ ፈተና ውስጥ እንደከተተው ነው የሚነገረው።

አቶ መሀመድ በኢትዮጵያ የደረሱት 256 የሳይበር ጥቃቶች በኤጀንሲው አማካኝነት ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርሱ መከላከል መቻሉን በበጎ ጎኑ ያነሳሉ።

ሀገሪቱ ታላላቅ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማስተናገድ መጀመሯ በቀጣይ ልትድርስብት ካሰበቸው እደገት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ይበልጥ ተጋላጭ እንድምትሆን መገመት አያዳግትም።

የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊው ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት በሰው ሀይል፣ በመረጃ እና በቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።

ኤጀንሲው በተለይም ለጥቃት ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ ተቋማት ጋር የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አንዳንድ የፋይናንስ ተቋማትም የራሳቸው የሳይበር ጥቃት መከላከያ ማዕከል እስከማቋቋም መድረሳቸውን አንስተዋል።

ከሳይበር ጥቃት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በማወቅ ረገድ በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረው ግንዛቤ ግን ገና አነስተኛ ነው።

የሳይበር ጥቃት ተከላካይ ባለሙያዎችን ከማፍራት አንፃር እንደ ሀገር ሰፊ ክፍተት መኖሩንም የሚያነሱ ምሁራን አሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምህሩ ዶክተር ኢሳያስ ገብረዮሀንስ፥ ሀገሪቱ እየገጠማት ላለው የሳይበር ጥቃት የመከላከል አቅም ለመፍጠር በቂ የሰለጠነ ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል።

የዶክተር ኢሳያስን ሃሳብ የሚጋሩት አቶ መሃመድ በሀገሪቱ ከሚገኙ 12 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት የጥናት እና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበርም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የሳይበር የትምህርት ዘርፍ ለመክፈት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖለጂ ኢንስቲትዩትን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት ዶክተር ኢሳያስ ገብረዮሃንስ፥ ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ዓመት ትምህርቱን መስጠት የሚያስችለውን የሰው ሃይል እና መሳሪያ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲም በተመሳሳይ ትምህርቱን ለመክፈት የሚያስቸለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው የመረጃ እና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ መለሰ ገብረየስ ተናግረዋል።

ሁለቱ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርቱን መስጠት ሲጀምሩ በሳይበር ተሰጥኦ ተቋም ብቻ ይሰጥ የነበረውን የትምህርት መስክ ከፍ በማድረግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልን ማሟላት ያስችላል።

ይህም በመስኩ የሚስተዋለውን ክፍተት በመሙላት የሳይበር ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

በተመስገን እንዳለ