የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያሳለፈው ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማሳነስ የሞከረ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ፓርላማ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ባሉት ዶክተር መረራ ጉዲና የፍርድ ሂደት ላይ ያወጣው መግለጫ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማሳነስ ከመሞከር የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ሀገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ እየሰራች የምትገኝና ለዚህ አበረታች ድጋፍ እየተሰጣት ባለበት ወቅት፥ የህብረቱ የህግ አውጪ አካል የሆነው የአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ካልተገነዘቡ አባላቱ እይታ ተነስቶ ያወጣው መግለጫ ስለመሆኑም አንስቷል።

ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም ህዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የህዝቡን ጥያቄ መመለስ እንደሚያስፈልግም ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ይህን ለመመለስ በመንግስት በኩል ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት መግለጫው መውጣቱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ላለው የትብብር መንፈስ ገምቢ አለመሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በህግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችን በተመለከተ የተሰጠው አስተያየትም የኢትዮጵያን የፍትህ አካሄድና ስርዓት ያላገናዘበ መሆኑም በመግለጫው ጠቅሷል።

ሚኒስቴሩ የህብረቱ ፓርላማ መግለጫ በሀገሪቱ የእድገት ጉዳይ ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ የሚያሳርፍ አለመሆኑንም ነው የጠቀሰው።

ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር እያሳደገች ላለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚመጥን፣ በመመካከር፣ በጋራ ጥቅም፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተና የሃገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ አመለካከት እንዲሰፍን፥ በተጠናከረ መልኩ ከህብረቱ ጋር ምክክሯን እንደምትቀጥልም አስታውቋል።