ግሪክ አዲስ የወጪ ቅነሳ ማዕቀፍ አፀደቀች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ግሪክ አዲስ የወጪ ቅነሳ ማዕቀፍ ማፅደቋ ተነግሯል።

የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ያፀደቁት አዲሱ የወጪ ቅነሳ ማዕቀፍ ለጡረታ የሚወጣው መጪ እንዲቀንስ የሚያደርግ ሲሆን፥ የታክስ ጭማሪ እንዲደረግ የሚያዝ ነው።

ከሀገሪቱ ወጪ ላይ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለመቀነስ ያለመው የወጪ ቅነሳ ማእቀፍም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2019 እና በ2020 ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

153 አባላት ያሉትና በጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፓራስ የሚመራው የግሪክ የጥምር መንግስት ፓርላማም በወጪ ቅነሳ ማዕቀፉ ላይ ሰፋ ያለ ክርክር ካደረገ በኋላ ማጽደቁ ተጠቁሟል።

የሀገሪቱ መንግስት ተቃዋሚዎች ግን የወጪ ቅነሳ ማዕቀፉን እንደማይደግፉ ያስታወቁ ሲሆን፥ በርካታ ግሪካውያንም የወጪ ቅነሳ ማእቀፉን ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል።

 

 

ምንጭ፦ አልጀዚራ