ፕሬዚዳንት ማክሮን ማሊ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲሱ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ማሊ ገብታዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በማሊ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ የፈረንሳይ የአየር ሀይል ማዘዣ ጣቢያ ማረፋቸው የተገለፀ ሲሆን፥ በዚያው የሀገሪቱን ወታደሮች ይጎበኛሉ ተብሏል።

ማክሮን በማሊ በሚኖራቸው አጭር ቆይታ ከፕሬዚዳንት ኢብራሂም ቡባካር ኬይታ ጋር እንደሚመክሩ ተገልጿል።

የፈረንሳይ ወታደሮች በቀድሞዋ የፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ሰሜናዊ ክፍል ከ2013 ጀምሮ ታጣቂዎችን እየተፋለሙ ይገኛሉ።

የመከላከያ ሚኒስትሯ ሲልቪያ ጉላርድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጄን ቬስ ለ ድሪያን ጋር ወደ ማሊ ያቀኑት ፕሬዚዳንት ማክሮን፥ ፈረንሳይ በአካባቢያው ያሰማራቻቸው 4 ሺህ ወታደሮች ባስመዘገቡት ውጤት ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንቱ በምዕራብ አፍሪካ የሚያራምዱት ወታደራዊ ፖሊሲ ከእርሳቸው በፊት እንደነበሩት ፕሬዚዳንቶች እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።

የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ሀላፊ ሬሚ ሪዮሃስ ከማክሮን ጋር ወደ ማሊ ማቅናታቸው ግን ፕሬዚደንቱ ኢኮኖሚያዊ ትብብሩን ማሳደግ እንደሚፈልጉ ያሳያል ተብሏል።

ፈረንሳይ ከአፍሪካ ጋር አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንድትከፍት እሰራለሁ በማለት ቃል የገቡት ኢማኑኤል ማክሮን፥ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ፈረንሳይ አልጀሪያን ቅኝ ለመግዛት ያደረገችው ጦርነት በሰብአዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ማክሮን በማሊ እያደረጉት ያለው ጉብኝት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ያደረጉት ሁለተኛው የውጭ ጉዟቸው ነው።

ፕሬዚዳንቱ ከበዓለ ሲመታቸው አንድ ቀን በኋላ ወደ ጀርመን አቅንተው ከመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ