የአዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ 57 በመቶ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ 57 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ከባቡር መስመሩ ግንባታ 57 በመቶው ተጠናቋል።

ፕሮጀክቱ አማራጭና ደረጃውን የጠበቀ የትራንስፖርት አገልገሎት በመስጠት የመጓጓዣ እጥረት ችግሩን እንደሚፈታ ገልጸዋል።

የባቡር ፕሮጀክቱ 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ለጭነትና ለመንገደኞች ማመላለሻ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር መስመር በመጭው ነሃሴ ወር መጨረሻም የሙከራ ስራ ይጀመራል ተብሏል።

በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚገነባው የአዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያ የባቡር መስመር ዝርጋታ በቱርክ ያፒ ሜርኬዚ ኩባንያ እየተገነባ ይገኛል።

በፕሮጀክቱ ሁለት ሃገር በቀል ተቋራጮችም በንዑስ ተቋራጭነት በመሳተፍ የአፈር ቆረጣና ሙሌት ስራውን እያከነወኑ ይገኛል።

እንዲሁም ከ4 ሺህ 200 በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል።

የባቡር መስመሩ በኤሌክትሪክ መስመር የሚሰራ ሲሆን፥ የኮንትራት ውሉ ሰኔ 19 2004 ዓ.ም መፈረሙ ይታወሳል።

ግንባታው ጥቅምት 8 2007 ዓ.ም የተጀመረው የባቡር ፕሮጀክቱ፥ 2011 ዓ.ም ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የባቡር ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 1 ነጥብ 7 ቢኒሊየን ዶላር ነው።


በይትባረክ ከበደ