የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 2፣ 2009 (ኤፍ. ቢ. ሲ) የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተመረቀ፡፡  

የመቀሌ ከተማና አካባቢው ነዋሪ፣ የውጭና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችና ሌሎች እንግዶች በፓርኩ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ታድመዋል፡፡

''እዚህ ቦታ ላይ ቆሜ ስናገር መርሳት የሌለብኝ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እያጣጣምን ያለነው ሰላም፣ ልማት እና ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን በተደረገው መራራ የትጥቅ ትግል፣ የትግራይ ህዝብ የከፈለውን መስዋእትነት ነው'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በምረቃ ስነስርዓት ላይ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኢትዮጰያ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ማምረት ስራ እየገቡ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሀገሪቱ በአፍሪካ የዘርፉ እምብርት ለመሆን የያዘችውን እቅድ እውን የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሀገሪቱ ለምታካሂደው የኢኮኖሚ ተሀድሶ ስኬት ፈር ቀዳጅ ናቸውም ነው ያሉት። 

ዛሬ የተመረቀው የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስም ካላቸው ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ፓርኩ የስራ እድል ከመፍጠርና የኢኮኖሚ እድገት ከማምጣት ባለፈ የአስተሳሰብ ባህልን የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

መሰረተ ልማት ሟሟላት፣ አቅም ያላቸውን የግል ባለሃብቶች መሳብና ወጣት ባለሃብቶችም ወደ ፓርኩ እንዲገቡ ማበረታታት ቀሪ የቤት ስራዎች መሆናቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይላማርያም የጠቀሱት፡፡ 

የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየደረጃው የሚገኙ አካላትም ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

mekele_industry_park_inag.jpg

ከመቐለ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ ሲሆን፥ ዛሬ የተመረቀው በ75 ሄክታር ላይ የተገነቡ 15 ሼዶች ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። 

ፓርኩ በቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን የተገነባ ሲሆን፥ ኤም ኤች ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት በአማካሪነት ስራውን መርቷል። 

በ92 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገነባው ፓርኩ፥ ከሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱ በ2025 የኢኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተናገሩት። 

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ዋና የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ መናኸሪያ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የወጪ ንግዱ ድርሻ ከፍ እንዲል ያደርጋልም ነው ያሉት። 

መሰረተ ልማት መዘርጋት ስኬት ቢሆንም በቀጣይ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የተመረጡ ባለሃብቶችን አስገብቶ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ማድረግ እና የሰው ሀይሉን በብቃት ማደራጀት እንደሚገባም አንስተዋል። 

mekele_industry_park_jpg.jpg

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አምባሳደር ዶክተር አዲስአለም ባሌማ በበኩላቸው፥ የክልሉ መንግስት ልዩ የኢንዱስትሪ ማበልፀጊያ ማዕከል በፓርኩ ውስጥ በማቋቋም የኢንዱስትሪ ፓርኩን በሰው ሀይል ለማጠናከር እየሰራ ነው ብለዋል። 

የውጭ ባለሃብቶች ወደ ፓርኩ ሲመጡ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ውጣውረዶች እንዲወገዱ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮች መጀመራቸውንም ገልፀዋል። 

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲጀመር በማድረግ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፥ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የአዋሽ ወልዲያ መቐለ የባቡር መስመር ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ እቁባይም፥ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቁ የሰው ሀይል እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አስገዶ በበኩላቸው፥ ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ስራ ሲገባ 20 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

በፓርኩ ውስጥ ለመስራት በርካታ የውጭ ሃገራት ባለሃብቶች ስምምነት መፈራራማቸውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባው ጠቁመዋል።

ሌሎች ባለሃብቶችም ፓርኩን ያለበት ሁኔታ ለመመልከት በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ መገኘታቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ አውስተዋል።