በምዕራብ አርሲ ዞን በተቀራራቢ ከተሞች በሕዝብ ትራንስፖርት የሌሊት ጉዞ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ቅሬታን ፈጥሯል

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የምእራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ አጭር ርቀትን ጨምሮ ከምሽት አንድ ሰዓት እስከ ማለዳ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ ማንኛዉም የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ ቁጥጥር እያደረገ ነዉ፡፡

ከሻሸመኔ እና ከሐዋሳ አቅራቢያ ከሚገኙ ከተሞች ለተለያዩ ስራዎች የህዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ነዋሪዎች የምዕራብ አርሲ የፖሊስ መምሪያ ሰሞናዊ እርምጃ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡

የፖሊስ መምሪያው ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ አይችሉም በሚል ቁጥጥር እያደረገ መሆኑ በኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን ነው ተጓዦቹ የሚናሩት፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም የቁጥጥር መመሪያውን መሰረት አድርገው የቀረቡለትን ቅሬታዎች ትክክለኛነት ለማጣራት የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያን ጠይቋል፡፡

የመምሪያው አዛዥ ኮማንደር ረታ በላቸው ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ህብረተሰቡን አሳፍረው በሌሊት ጉዞ የሚያደርጉ ተሸከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮማንደር ረታ የቁጥጥሩ ዓላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እና የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ ነው ይላሉ፡፡

ስለቀረቡት ቅሬታዎች ኮማንደሩ ሲናገሩ የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ እና የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ቁጥጥሩን አጠናክሮ የማስቀጠል አቋም አለን ነው ያሉት።

በዚህም መሰረት አደጋው የሚበዛበት ሰዓት ተጠንቶ ሊሻሻል ወይም የበለጠ ሊጠብቅ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የስራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር አለሙ መግራ በበኩላቸው፥ የቁጥጥር መመሪያው የረዥም ርቀት ተጓዦችን ለመቆጣጠር የወጣ እንጂ

በተቀራራቢ ከተሞች የሚደረጉ የአጫጭር ርቀት ጉዞዎች ላይ የሚተገበር አይደለም ብለዋል፡፡

ለአብነትም ከሃዋሳ-ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ-ሻሸመኔ፣ ከኮፈሌ-ሻሸመኔ የሚደረጉ ጉዞዎች የቅርብ ርቀት ጉዞ በመሆናቸው፥ በቀድሞው የጉዞ ሰዓት መጓዝ እንደሚችሉ እና በአዲሱ መመሪያ ቁጥጥር እንደማይደረግባቸው ለምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ እንደተገለፀለትም ገልጸዋል።

ይህም በቅርብ ባሉ ከተሞች ተጉዘው የሚሰሩ እና የሚማሩ ሰዎች መኖራቸውን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

ኮማንደር አለሙ በምዕራብ አርሲ ዞን ተቀራራቢ ከተሞች የታየው የምሽት ትራንስፖርት መጉላላትና የህዝቡ ቅሬታ እንዲቀረፍ ትዕዛዝ መተላለፉንም አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥሩ መደረግ ያለበት በረጅም ርቀት ተሸከርካሪዎች ላይ ብቻ እንደሆነ ጠቅሶ፥ ተመጋጋቢ እና ተቀራራቢ ከተሞችን የሚመለከት ባለመሆኑ ዞኑ ማስተካከያ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ብቻ 85 ሞት የተመዘገቡባቸው የትራፊክ አደጋዎች መከሰታቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡

 

 

 

 

በብርሃኑ በጋሻው