ፈረንሳይ የባህረ ሰላጤው ሀገራት በኳታር ዜጎች ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 8፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ የባህረ ሰላጤው ሀገራት የገቡበትን ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ለማርገብ በኳታር ዜጎች ላይ የተጣለው ማዕቀብ መነሳት እንዳለበት ጠይቃለች፡፡

ኳታር እና ስድስት የባህረ ሰላጤው የዓረብ ሀገራት በመካከላቸው የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ መሻከር ለማለሳለስ መስራት እንዳለባቸው ጠቁማለች፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ዩናይትድ ኣረብ ኢምሬትስ፣ ባህሬን እና ግብፅ ከፈረንጆቹ ሰኔ 5 ቀን ጀምሮ የተለያዩ ማዕቀቦችን በኳታር ላይ መጣላቸው ይታወቃል፡፡

ሀገራቱ ማዕቀቡን በኳታር ላይ የጣሉት የሺብር ቡድኖችን በገንዘብ ትደግፋለች በሚል ነው፡፡

ዶሃ ግን በተቃራኒ ጎራ ቆመው ዲፕሎማሲዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጡ ሀገራት የሚሉትን ውንጀላ አጣጥለዋለች፡፡

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዥያን ይቭ ለ ድርያን በኳታር ዜጎች ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳርፉ ማዕቀቦች በተቻለመጠን በአፋጣኝ ሊነሳ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከኳታሩ አቻቸው ሼክ ሞሃመድ ቢን አብዱራህማን አል ታኒ ጋር በዶሃ ውይይት አድርገዋል፡፡

ለ ድሪያን ከኳታሩ ጉብኝታቸው ቀጥሎ ዛሬ አመሻሽ ሳዑዲ የሚገቡ ሲሆን፥ በነገው ዕለት በዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በፊት የባህረ ሰላጤው ሃገራት ዲፕሎማሲዊ ቀውስ እንዲፈታ ኩዌት ጥረት እያደረገች ሲሆን፥ በዚህ ሳምንት ውስጥ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመሳሳይ አቋም ማንፀባረቃቸው ይታወሳል፡፡

ቲለርሰን ከኳታሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልታኒ ጋር የሽብር ቡድኖችን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ስምምት ተፈራርመዋል፡፡
ሳዑዲን ጨምሮ አራት የዓረብ ሀገራት በበኩላቸው በዶሃ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ተፈጻሚነት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

 

ምንጭ፡-ሬውተርስ