በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን አረም እና ሁሉን አውዳሚ ተምች ለመከላከል ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን መጤ አረም እና ሁሉን አውዳሚ የተምች ተባይ ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ ተገለጸ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው መደበኛ ስብሰባው፥ እነዚህ ተፈጥሮን የሚጎዱ ክስተቶች በቀላሉ ሊታዩ እንደማይገባ አሳስቧል።

በሀይቁ ላይ የተከሰተውን መጤ አረም ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም ባለበት እንዲቆምና፥ በቀጣይ ስጋት እንዳይሆን ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት አፋጣኝ የመፍትሄ ሀሳቦችን ሊያቀርቡ ይገባል ተብሏል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ የተሰበሰበው የገቢ መጠንን የገመገመ ሲሆን ከእቅዱ አንጻር ደካማ አፈጻጸም ቷይቷል ብሏል።

የውሀ፣ የመንገድ፣ የመብራትና መሰል የመሰረተ ልማት ስራዎች አፈጻጸም በቀጣይ ሊሻሻል እንደሚገባውም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይም የተደራጁ ማህበራትን የመከታተልና የመደገፍ ሂደቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያለው።

ምክር ቤቱ በቀጣዮቹ ቀናት በሚኖረው ስብሰባ ሌሎች አጀንዳዎችን ተመልክቶ እንደሚያጽቅ ይጠበቃል።


ዘገባውን የጎንደር ፋና ኤፍ ኤም ባልደረባችን ሙሉጌታ ደሴ አደርሶናል።