እስራኤል የሶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደምትቃወም አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአሜሪካ፣ ሩስያ እና ዮርዳኖስ አደራዳሪነት በደቡባዊ ሶሪያ የተኩስ ልውውጥ እንዳይኖር የተደረሰውን ስምምነት እንደሚቃወሙ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያይተዋል።

ኔታንያሁ ከማክሮን ጋር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ ቴል አቪቭ በደቡባዊ ሶሪያ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነትን ሙሉ በሙሉ ትቃወማለች ብለዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ኢራን በድንበር አካባቢ ሀይሏን የበለጠ እንድታስፋፋ የሚያግዝ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ኔታንያሁ ትናንት ማምሻውን በዚሁ የተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ጋር በስልክ መምከራቸው ተገልጿል።

ቴል አቪቭ ከዋሽንግተን እና ሞስኮ ጋር ያላት አለመግባባት በሰከነ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ብቻ እንደሚፈታም ተናግረዋል።

አንድ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣንም ኢራን በሶሪያ ሰፊ ወታደራዊ ሀይል ለማሰማራት እንዲሁም የአየር እና የባህር ጣቢያ እንዲኖራት ትሻለች ማለታቸው ተጠቁሟል።

አሜሪካ፣ ሩስያ እና ዮርዳኖስ ከ10 ቀናት በፊት (ሀምሌ 7 2017) በደቡባዊ ሶሪያ ደራ፣ ሱዋይዳ እና ኩኔትራ ግዛቶች የተኩስ ልውውጥ እንዳይኖር እና ከጦርነት ነፃ የሆነ ቀጠና እንዲመሰረት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ይህ ስምምነትም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩስያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በጀርመን ሀምቡርግ ከተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ጎን ለጎን በመከሩበት ወቅት ነው ይፋ የሆነው።

ባለፈው ሳምንትም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈፃሚ መሆን መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የሶሪያ መንግስት እስራኤል ከምዕራባዊያን እና ከቀጠናው አጋሮቿ ጋር በመሆን የታክፊሪ ታጣቂ ቡድንን ትደግፋለች በማለት ይወቅሳል።

ቴል አቪቭ በሶሪያ መንግስት ወታደሮች በተያዙ የጎላን ተራራ አካባቢዎች ላይ የአፃፋ ምላሽ ነው በሚል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝራለች።

ደማስቆ በበኩሏ የጥቃቶቹ ዋና አላማ የሶሪያ መንግስትን እየተዋጉ የሚገኙትን የታክፊሪ ታጣቂዎች መደገፍ ነው ስትል ትወቅሳለች።

የሶሪያ ጦር በተለያዩ ጊዜያት ከተቃዋሚ ሀይሎች በእስራኤል የተሰሩ የጦር መሳሪያዎችን መማረኩ ይነገራል።

እስራኤል በሶሪያ በጦርነት ወቅት ጉዳት ለሚደርስባቸው ታጣቂዎች የህክምና ድጋፍ ታደርጋለች የሚሉ መረጃዎችም ወጥተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም ከቅርብ ወራት ወዲህ የእስራኤል ወታደራዊ ሀይል እና የሶሪያ ታጣቂዎች የመሰረቱት ግንኙነት ቸል ሊባል አይገውም ማለታቸው አይዘነጋም።

 

 

 

ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ