የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የኳታር የዜና አገልግሎት ድረ ገፅን ጠልፋለች መባሉን አስተባበለች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ባለፈው ግንቦት ወር በኳታር ብሄራዊ የዜና አገልግሎት ድረ ገፅ ጠለፋ ጀርባ አለች መባሉን ውድቅ አደረገች።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ጋርጋሽ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፥ ከመረጃ ጠለፋው ጋር የሚናፈሰው መረጃ ሀሰት ነው ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስን ጨምሮ አምስት የአረብ ሀገራት ኳታር የ2022ቱን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ የተሰጣትን እድል እንድትነጠቅ ጠይቀዋል በሚል በተለያዩ ድረ ገፆች የወጣው መረጃም ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘ ሎካል የተባለው የስዊዘርላንድ የዜና ወኪል የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አምስት የአረብ ሀገራት ኳታር የ2022ቱን የአለም ዋንጫ እንዳታስተናግድ ጠይቀዋል የሚል መረጃን ይዞ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

በሌላ በኩል ዋሽንግተን ፖስት የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናትን ጠቅሶ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የኳታሩ ኤሚር አሉት ተብሎ በስህተት እንዲወጣ የተደረገውን ዘገባ አቀነባብራለች ማለቱ አይዘነጋም።

ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው ግንቦት 23 2017 የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ባለስልጣናት የኳታር ብሄራዊ የዜና ወኪልን ድረ ገፅ ለመጥለፍ ማቀዳቸውን ስማቸው ካልተጠቀሰ የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣን መስማቱን ገልፀዋል።

በቀጣዩ ቀን የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አል ታህኒ አሜሪካ ለኢራን ክፉ ናት ማለታቸውንና ዋሽንግተን ቸል ልትባል በማይገባት እስላማዊ ሀያል ሀገር ላይ የያዘችው አቋምን መንቀፋቸውን የሚገልፅ መረጃ በሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት ድረ ገፅ ላይ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

ሀማስ “የፍልስጤም ህዝቦች ህጋዊ ተወካይ ነው” ብለዋል የሚለውም በድረ ገፁ ላይ ወጥቶ ነበር፤ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ቢነሳም።

ይህ መረጃ መውጣቱን ተከትሎም የኳታር ባለስልጣናት የዜና አገልግሎቱ ድረ ገፅ ማንነታቸው ባልታወቁ የመረጃ ዘራፊዎች መጠለፉንና መረጃው ትክክል እንዳልሆነ ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ መረጃው በስፋት ተሰራጭቶ በቀጠናው ሀገራት መካከል አለመግባባት ፈጥሯል።

ኤሚሩ ኢራንን ማወደሳቸው እና ሀማስን መደገፋቸውን የሚያሳየው መረጃ በስፋት መሰራጨቱ ያበሳጫቸው የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን እና ግብፅም የኳታር መገናኛ ብዙሃንን በመዝጋት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ከሁለት ሳምንት በኋላም አራቱ ሀገራት ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል ከኳታር ጋር የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጠዋል።

የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት የኳታር ብሄራዊ የዜና አገልግሎት ድረ ገፅን የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ መንግስት ራሱ ይጥለፍ አልያም ስራውን በሶስተኛ ወገን በኩል ያከናውነው ግልፅ አላደረጉም።

ዘጋርዲያን በበኩሉ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ከመረጃ ጠለፋው ጀርባ የሩስያ ተቀጣሪ የመረጃ ዘራፊዎች እንዳሉ አረጋግጫለሁ ማለቱን ዘግቧል።

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ