ኢራን አሜሪካ የእስላማዊ አብዮት ዘብ አባላትን በሽብር መዝገብ እንዳታሰፍር አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራን አሜሪካ የእስላማዊ አብዮት ዘብ አባላትን በሽብር መዝገብ ውስጥ እንዳታሰፍር ማስጠንቀቋ ተሰማ።

የኢራን መከላከያ ኤታማጆር ሹም ሜጀር ጀኔራል ሞሃመድ ባቃሪ የአሜሪካ ሴናተሮች ኢስላሚክ ሪቮሊዩሽን ጋርድስ ኮርፕስን (አይ አር ጂ ሲ) በሽብርተኛ ድርጅት ስም ለማስፈር እያደረጉት ያለው አካሄድ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው ብለዋል።

ኢራናውያንን ኢላማ ያደረጉ ማዕቀቦችን ለመጣል መታቀዱም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልፀዋል።

ጀኔራሉ የእስላማዊ አብዮት ዘብ የቴህራንን ህልውና ለመጠበቅ ይንቀሳቀሳል እንጂ በማንም ሀገር ጣልቃ አይገባም ብለዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በቅርቡ እንደገለጹት አሜሪካ በኢራን ሰላማዊ የአስተዳደር ለውጥ እንዲኖር ድጋፍ እንደምታደርግ እና ዋሽንግተን ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ መምጣቱን መግለፃቸው ይታወሳል።

አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ያሰብኩት ቴልአቪቭ አጠቃላይ የሚሳኤል ፕሮግራሟን በመቀጠሏ፣ እንደ ሄዝቦላህ ያሉ ተፋላሚ ቡድኖችን በመደገፏ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀመች በመሆኑ ነው ብላለች።

ቴህራን ግን ይህን የዋሽንግተን ውንጀላ አትቀበለውም።

 

 

ምንጭ፦ ፕሬስ ቲቪ