የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ 5ኛ አመት መታሰቢያ አስተምህሮቶቻቸውን በሚያስቀጥሉ ዝግጅቶች ዛሬ መከበር ጀምሯል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ 5ኛ አመት መታሰቢያ ቀን አስተምህሮቶቻቸውን በሚያስቀጥሉ የተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ መከበር ጀምሯል

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አምስተኛ አመት መታሰቢያ መለስ በህይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ እና እንደ አህጉርም ለአፍሪካ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በሚዘክር መልኩ እንደሚከበር የመለስ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ተናግረዋል።

በአከባበሩ ታላላቅ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ምሁራን የሚሳተፉበት የምክክር መድረክን ጨምሮ፥ የእርሳቸውን በጎ ትሩፋቶች እና ህይወታቸውን የሚያስቃኝ አውደ ርዕይም የዝግጅቱ አካል ነው።

የመለስ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን አምስተኛ አመት መታሰቢያ መርሃ ግብሮችን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ አቶ መለስ ያገለገሏት እና ህይወታቸውን የሰውላት ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄር ብረሰቦች እኩል ሀገር የማድረግ ተጋድሎን ለመዘከር በመለስ መታሰቢያ ፓርክ የብሄር ብሄረሰቦች ውክልናን የሚሳይ መተላለፊያ የእግረኛ መንገድ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ይቀመጣል።

አቶ መለስ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማንነታቸው ታውቆ እና ተከብሮ የራሳቸው በሆነች ሀገር ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የፌደራል ስርዓትን ከትግል ጓዶቻቸው ጋር የቀየሱ እና ለውጤት ያበቁ ናቸው።

ይህን ትሩፋታቸውን ለማስቀጠልም የታላቁ መሪ በአዲሲቷ ፌዴራላዊ ኢትዮጵያ ምስረታ የመሪነት ሚና ይወሳል ነው ያሉት።

ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ሀገሪቱ የወጣቶች መሆኗን ሰብከዋል፤ የሀገሪቱ ጠላት የሆነው ድህነትን ከስሩ መንቀል የሚቻለው በወጣቶች ክንድ መሆኑንም በተደጋጋሚ ማንሳታቸው ይታወሳል።

በአምስተኛ አመት መታሰቢያ መርሃ ግብርም ይህንን የመለስ አስተምህሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ወጣቶችን የሚያነቁ ፕሮግራሞች ይኖራሉ ነው ያሉት ወይዘሮ አዜብ።

በመግለጫቸው የተለያዩ ፅሁፎች ቀርበው የፓናል ውይይት እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና መቻቻል፣ በፌደራሊዝም፣ በወጣቶች እና ሴቶች እንዲሁም በአረንጎዴ ልማት ዙሪያ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፋቸው ያቀርባሉ ብለዋል።

ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ከትግል ጀምሮ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ጨምሮ በርካታ ፅሁፎችን እንዳበረከቱ የሚናገሩት ወይዘሮ አዜብ፥ ከ400 በላይ ሰነዶች ተሰብስበው ወደ ሶፍት ኮፒ መቀየራቸውን አንስተዋል።

ከእነዚህ ውስጥም በተለያዩ ጉዳዮች ታላቁ መሪ መለስ የጻፏቸዉን አምሰት ስትራቴጂካዊ ሰነዶችን፥ በመታሰቢያ ቀኑ ለማድረስ ለህትመት የማቅረብ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

ታላቁ መሪ መለስ ያረፉበት 5ኛ አመት መታሰቢያ ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር የጀመረ ሲሆን፥ የስፖርታዊ ውድድሮች፣ ችግኝ ተከላ፣ የኪነጥበብና ዝግጅትና አውደ ርዕይ የመታሰቢያው አካል ናቸው።

በዛሬው ዕለትም '' የዘመን ክስተት መለስ ዜናዊና አዲሲቷ ኢትዮጵያ'' የተሰኘ መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተመርቋል።

በደራሲ ገብረሚካኤል ገብረማርያም የተፃፈው ይህ መጽሐፍ የደራሲው 2ኛ ስራ ሲሆን በ13 ምዕራፎች ተደራጅቶ የተዘጋጀ ነው።

የስድስት ዓመት ዝግጅትን የጠየቀው መጽሐፉ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ዘመን በኢትዮጲያ የተደረጉ ሽግግሮችና ትውልዱ ከመለስ አስተምህሮዎች ሊማር የሚገባቸው ጉዳዮች ተዳሰዋል።

በመፅሃፉ ምረቃ ላይ የቀድሞ የኢፌሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት  ወይዘሮ አዜብ መስፍን፣ የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የመፅሃፉን መመረቅ በይፋ ያበሰሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስራው መነሻ መሆኑን አንስተው፥ ''መለስ ትልቅ ቤተ መፅሃፍት ናቸው፤ ስለመለስ የሚደረጉ ጥናቶችም ሊቀጥሉ ይገባል" ብለዋል።

 

 

 

 

 

በተመስገን እንዳለ በበርናባስ ተስፋዬ

 

'' የዘመን ክስተት መለስ ዜናዊና አዲሲቷ ኢትዮጵያ'' የተሰኘው መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተመርቋል።

 

በደራሲ ገብረሚካኤል ገብረማርያም የተፃፈው ይህ መጽሐፍ የደራሲው 2ኛ ስራ ሲሆን በ13 ምዕራፎች ተደራጅቶ የተዘጋጀ ነው።

 

የስድስት ዓመት ዝግጅትን የጠየቀው መጽሐፉ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ዘመን በኢትዮጲያ የተደረጉ ሽግግሮችና ትውልዱ ከመለስ አስተምህሮዎች ሊማር የሚገባቸው ጉዳዮች ተዳሰዋል።

 

በመፅሃፉ ምረቃ ላይ የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን፣ የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የመፅሃፉን መመረቅ በይፋ ያበሰሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስራው መነሻ መሆኑን አንስተው፥ ''መለስ ትልቅ ቤተ መፅሃፍት ናቸው፤ ስለመለስ የሚደረጉ ጥናቶችም ሊቀጥሉ ይገባል" ብለዋል።

 

በበርናባስ ተስፋዬ