ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ ፕሬዚዳንት በመሆን በድጋሚ ተመረጡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባሳለፍነው ማክሰኞ በኬንያ በተደረገው ምርጫ ሀገሪቱን በመምራት ላይ የነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ በድጋሚ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ከ2013 ጀምሮ ኬንያን በመምራት ላይ የነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ በማክሰኞ እለት በተካሄደው ምርጫም 54 ነጥብ 3 በመቶ ድምፅ በማግኘት መመረጣቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

ተፎካካሪያቸው የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ 44 ነጥብ 7 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ውጤቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፥ አንድ እንሁን የሚል ምልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የተቃዋሚ ፓርቲ ዳጋፊዎችንም “ለእናንተም አለውላችሁ፤ እኛ የአንድ ሪፐብሊክ ዜጎች ነን” ብለዋል።

ተቃዋሚዎች ግን የምርጫ ውጤቱን አንቀበልም ያሉ ሲሆን፥ የምርጫው ውጤትም ተጭበርብሯል የሚል አቋም ነው ያላቸው።

ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው ፍትሃዊ እንደነበር ማረጋገጣቸው ነው የተነገረው።

ይህንን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፥ “ነፃ፣ ግልፅ እና ታማኝ የሆነ ምርጫ ማድረጋችንን አረጋግጠናል” ብለዋል።

የምርጫውን አንቀበልም ያሉት ተቃዋሚዎች በኪስሙ ከተማ ውስጥ አመፅ ማስነሳታቸውም ተነግሯል።

የኬንያ ፖሊስም አመፅ የቀሰቀሱ ሰዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ የተነገረ ሲሆን፥ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን የጦር መሳሪያ ተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበረ እማኞች ተናግረዋል።

ራይላ ኦዲንጋ አሸንፈዋል በሚል ተቃሚዎች ቀደም ብለው የራሳቸውን ቁጥር ይፋ አደርገው የነበረ ሲሆን፥ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ግን ይህ ህገ ወጥ ተግባር ነው ማለቱ ይታወሳል።

በኬንያ የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ እየነገሰ ያለው ውጥረት ከ10 ዓመት በፊት ከምርጫ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ የነበረው ግጭት ዳግም እንዳይቀሰቀስ ስጋት ፈጥሯል።

በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ግጭትም 1 ሺህ 100 ኬንያውያን ለህልፈት የዳረገ ሲሆን፥ 600 ሺህ ኬንያውያን ደግሞ ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ ማድረጉ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ