ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮርያን አስጠነቀቁ

ሰሜን ኮርያ የዩናይትድ ስቴትስ የፓሲፊክ ግዛት በሆነው ጉዋም ላይ የሚሳይል ጥቃት ለመክፈት አስቤያለው ማለቷ ከአሜሪካ ቁጣን አስከትሎባታል።

የአሜርካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፦ በአሜሪካ ግዛት ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ዓይነት ጥቃት “አፀፋዊ ምላሽ ያገኛል” የሚል ማስጠንቀቅያም ሰጥተዋል።

ሰሜን ኮርያ ከድርጊትዋ ካልተቆጠበች ልላ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንደሚጠብቋትም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

የቻይና ቴሌቪዥን እንዳሳወቀው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ በሁለቱም ሀገራት ለተፈጠረው ግጭት ወደ ፍፁም ሰላም እንዲመልሱት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተማፅነዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ በበኩላቸው ሁለቱም አካላት የሚሰነዝሩት አስጊ ተግባርና የቃላት ምልልስ ማስወገድ እንዳለባቸው በማሳሰብ፤ አሜሪካና ቻይና የሰሜን ኮርያ የሚሳይል ቦምብ ለማስቆም የጀመሩት ጥረት እንደሚቀጥሉበት አሳውቀዋል፡፡

የዋይት ሀውስ መንግስት በበኩሉ ዩናይትድ ስቴትስና የፕዮንግያንግ መንግሥት መስማማት እንዳለባቸው በማሳሰብ በተለይ ሰሜን ኮርያ ከጠባጫሪ ባህሪዋ መቆጠብ እንዳለባት ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ድምፀት ባለው አነጋገር፥ "በእርግጠኝነት ለመናገር ከፕሬዚዳንት ትራምፕ በላይ ሰለማዊ መፍትሔ የሚፈልግ የለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ወራት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮርያ የጀመረችውን ማንኛውንም የኒኩሌር መርሃ ግብር አጋርዋ ቻይና እንድታስቆም ካላደረገች ዩናይትድ ስቴትስ በራስዋ ታስቆማታለች ሱሉ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

በደስታ ተካ