ግብፅ ውስጥ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው በትንሹ 49 ሰዎች ሞቱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ ውስጥ በአሌክሳንድሪያ ከተማ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው በትንሹ የ49 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው፡፡

በከተማዋ ዳርቻ የኮርሺድ ባር ጣቢያ አካባቢ ሁለት ባቡሮች እርስ በእርስ ተጋጭተው ነው አደጋው የደረሰው፡፡

በዚህም ከሟቾች ባሻገር ከ133 በላይ ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የግብፅ ጤና ሚኒስትር ዲኤታ ሄጋዚ ማግዲ ገልፀዋል፡፡

ተጎጅዎችን ወደ ህክምና ተቋማት ለማድረስም 30 አምቡላንሶች በስፍራው መሰማራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትር ሂሻም አራፋት በበኩላቸው፥ አደጋው የተፈጠረው በባቡር ሰራተኞች ስህተት ነው ቢሉም፥ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የአደጋዎችን የጉዳት መጠን ለመቀነስ ወደፊት የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማሻሻል እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

በግብፅ የባቡር መስመሮች የጥራት ችግር እንዳለባቸውና መንግስትም አደጋውን ለመቀነስ ማሻሻያ አልሰራም በሚል ይተቻል፡፡

በሀገሪቱ ከዚህ በፊት በ2013 19 ሰዎች የሞቱበትና 103 ሰዎች የተጎዱበት፣ በ2015 ወደ ትምህርት ቤት የሚጓዙ ህጻናትን ያሳፈረ አውቶብስ በባቡር

ተገጭቶ 7 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈበት እና በ2016 በካይሮ በርካቶች ለህልፈት የተዳረጉበትን ጨምሮ በርካታ የባቡ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡

 

 

 

 

ምንጭ፡-አናዶሉና አልጀዚራ