የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን ጥሏል።

ፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ሙከራን ለስድስተኛ ጊዜ ማድረጓን ተከትሎ አሜሪካ ያቀረበችውን ረቂቅ የማዕቀብ የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

ሩሲያና ቻይናን ጨምሮ 15 አባላት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ማዕቀብ ሰሜን ኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ወደ ውጭ እንዳትልክና ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የዘይት ምርቶችን እገዳ የሚጥል ነው።

እገዳው ሁሉንም ድፍድፍ እና የተጣራ ተፈጥሯዊ የነዳጅ ዘይቶች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ የሚከለክል ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ሁሉም ሀገሮች ለሰሜን ኮሪያ ሰራተኞች አዲስ የሥራ ፈቃድ እንዳይሰጡ የሚከለክል እገዳ የተጣለ ሲሆን፥ ይህም በሀገሪቱ ሁለት ዋና ዋና የገቢ ምንጮች ከባድ ጫና የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል።

ሆኖም ማዕቀቡ ፒዮንግያንግ ባለፉት 12 ወራት ከውጭ ያስገባችውን የነዳጅ ዘይት ያህል ብቻ ሊቀንስ የሚችል ሲሆን፥ በዓመት ከውጭ የምታስገባው የተጣራ የነዳጅ ምርት ወደ 2 ሚሊየን በርሜል ዝቅ እንዲል ነው የሚያደርገው።

አሜሪካ መጀመሪያ ያቀረበችው ጥያቄ በሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ሃብት ንብረት እና ሀገራት ለሰሜን ኮርያ የዘይት ሽያጭ እንዳይፈፅሙ ሙሉ በሙሉ እገዳ እንዲጣል ነበር።

ነገር ግን ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት አስቀድመው ከአሜርካ ጋር ባደረጉት ድርድር የእርምጃ ለውጥ መደረጉ ተነግሯል።

እገዳው በፈረንጆች ከ2006 ጀምሮ የባሊስቲክ ሚሳኤል እና የኒዩክሌር መርሃ ግብሮች ላይ የቀረበ ዘጠነኛ ማዕቀብ ነው ተብሏል። 

 

ምንጭ፦ አልጀዚራ