ፖሊስ በሙስና ጠርጥሮ ባለፉት ቀናት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የስራ ሀላፊዎች ዛሬ ፍርድ ቤት አቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል ፖሊሰ በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ጵጉሜን 3 እና 4 በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከፍተኛ የስራ ሀላፊ አትክልት ተስፋዬ እና የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ደጉ ላቀው ዛሬ ፍርድ ቤት አቀረበ።

ተጠርጣሪዎቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው የቀረቡት።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ደጉ ላቀው የትራንስ ናሽናል የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር የነበረው የፕሮጀክት ውል መጠናቀቁን እያወቀ ኩባንያው ከውጪ ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸውን ስምንት ተሽከርካሪዎች “የመስሪያ ቤቱ የፕሮጀክት ስራ ነው” በሚል መንግስት ያገኝ የነበረውን 10 ነጥብ 5 ሚሊዬን ብር በማሳጣት መጠርጠሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ዛሬ በእነ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ ያሉ 16 ተጠርጣሪዎች ምርመራ አጠናቆ ለአቃቢ ህግ አስረክቧል።

ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግም የጠየቀውን የክስ መመስረቻ የ11 ቀን ተጨማሪ ጊዜ በመስጠት የሚኒስትር ዴኤታው አማካሪ ደጉ ላቀው ጉዳይ ከመዝገቡ ጋር እንዲጣመር አዟል።

በችሎቱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከፍተኛ የስራ ሀላፊ አትክልት ተሰፋዬ ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን 20 ሚሊዬን ብር የሚገመት ጠጠርና የአርማታ ብረት ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ በማዋስ እና ሳይመለስ በመቅረቱ ተመሳሳይ መጠን ያለው የብር ጉዳት በመድረሱ መጠርጠሩ ተገልጿል።

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪው ጉዳይ በነገው ዕለት በእነ አበበ ተስፋዬ መዝገብ ጋር ተጣምሮ እንዲቀርብ አዟል።

በተጨማሪም ችሎቱ አቃቤ ህግ ክሱን አጠናቆ እንዲቀርብ የታዘዘበት የእነ ፀዳለ ማሞ የክስ ጉዳይ፥ ክሱን አቃቤ ህግ አጠናቆ ባለመቅረቡ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በአምስት ቀን ተጠናቆ እንዲቀርብ የፊታችን አርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።


በታሪክ አዱኛ