በአዋሽ ወንዝ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ተፋሰሱን ተከትለው ባሉ የኦሮሚያ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ ተደረገ።

የውሃ ሙላቱ በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት ባያደረስም በእንሰሳትና በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየጣለ ሲሆን፥ ዝናቡ ከፍተኛ መጠን ያለው በመሆኑ የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ እንዲሞላ አድርጎታል።

የወንዙ መሙላት ተፋሰሱ የሚያልፍባቸው የተወሰኑ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አሁን ላይ በውሃ  እንዲዋጡ አድርጓቸዋል።

በተለይም በበፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ሀዋስ የወንዙ ሙላት በተፋሰሱ አካባቢዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ገረመው ኦሊቃ፥ ሰበታ ሀዋስ አካባቢ የአዋሽ ወንዝን ተጠግተው በርካታ ነዋሪዎች የሚኖሩ በመሆኑ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ጉዳት ሳይደርስባቸው አካባቢያቸውን እንዲለቁ መደረጉን ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹን ከአካባቢያቸው ለማስወጣት በተደረገው ጥረት በሰው ላይ ጉዳት ባይደርስም በእንሰሳትና በሰብል ላይ ግን ጉዳት መድረሱን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር አቶ ገረመው፥ አሁን ላይ ውሃው በሰብልና በእንሰሳት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

አካባቢያቸውን ለቀው ተፍኪ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች የምግብ እና የጤና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ገረመው ተናግረዋል።

ጉዳት ያልደረሰባቸው አካባቢ ነዋሪዎች በተለይም የተፍኪ እና የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች ለተጎጅዎች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የተረጂዎች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ በመምጣቱ ከዛሬ ጀምሮ ተጨማሪ እርዳታዎች ይደረጋሉ ብለዋል።

በወንዙ ሙላት ምክንያት በተዘራ የሰብል ማሳ ላይም ጉዳት መድረሱን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ የደረሰውን ጉዳት የሚለይ አካል ተቋቁሞ በአጭር ቀናት ውስጥ በሚያቀርበው ሪፖርት መሰረት የክልሉ መንግስት ለአርሶ አደሮች ዘር ያቀርባል ብለዋል።

በጎርፉ ምክንያት በነዋሪዎች ቤት ላይ ጉዳት የደረሰ በመሆኑ በቀጣይ ነዋሪዎችን የማቋቋሙ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

የአካባቢው ነዋሪዎች እገዛን ያደነቁት አቶ ገረመው፥ ከአካባቢው አቅም በላይ ለሆኑ ችግሮች ሁሉ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሚቀጥሉት ቀናት የአዋሽ ወንዝ ሙላት ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳትን ለመቀነስ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የብሄራዊ አደጋ ሰጋት አመራር ኮሚሽንም አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰፍሩ ለተደረጉ ዜጎች የምግብና አስፈላጊውን የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረኩ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን ለዜጎች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

 

የአዋሽ ተፋሰስ ባለስላጣን በበኩሉ፥ በአዋሽ ወንዝ ሙላት ምክንያት ተፋሰሱን ተከትለው ባሉ የኦሮሚያ ወረዳዎች የተከሰተው ጎርፍ መጠን እየቀነሰ መሆኑን አስታውቋል።

 

የአዋሽ ተፋሳሰስ ባለስልጣን የሜትሮሎጅ መረጃዎች እንደ ሚያሳዩት በአካባቢው ሲጥል የነበረው ዝናብ እየቀነሰ መጥቷል ይላል።

 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው፥ የዝናብ መጠኑ መቀነስ በሰበታ ሀዋስ፣ ሎሚ እና ኢሉ ወረዳዎች የተከሰተው ጎርፉ ከዛሬ በፊት ከነበሩት ቀናት ከነበረው መጠን እየቀነሰ መሆኑን ይናገራሉ።

 

የዝናቡም ሆነ የጎርፍ መጠኑ ቢቀንስም አሁን በተፋሱሱ አካባቢዎች ስጋቶች አሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው፥ ከቆቃ የሀይል ማመንጫ ግድብ እየተለቀቀ ያለው የውሀ መጠን ከፍተኛ መሆን ስጋቱ ከፍተኛ አድርጎታል ብለዋል።

 

ሆኖም በሚቀጥሉት ቀናት በጎርፉ ምክንያት አደጋዎች እንዳይደርሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብሏል።

 

የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን አሁን ላይ የዘናቡ መጠን እየቀነሰ ቢሆንም የወንዙ ሙላት ከፍተኛ በመሆኑ በተፋሰሱ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል ብሏል።

 


በንብረቴ ተሆነ