የባህረ ሰላጤው አገራትና የኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግጭት በአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ጎልቶ ታይቷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግብፅ ካይሮ ትናንት በተካሄደው የአረብ ሊግ አገራት ጉባኤ ላይ በኳታር እና ዶሃን ባገለሉ የባህረ ሰላጤው አገራት ተወካዮች መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት የአገራቱ ልዩነት እየሰፋ ለመምጣቱ ማሳያ ሆኖ አልፏል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ግብፅና ባህሬን ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት በይፋ ካቋረጡ ወራት ተቆጥረዋል።

አገራቱ የዲፕሎማሲ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ከማቋራጥ ባለፈ ወደ ዶሃ የሚደረጉ የዓየር በረራዎች እና የባህር ትራንስፖርቶችን በክልልቸው እንዳይደረጉም አግደዋል።

ለዚህ ሁሉ መነሻቸው ኳታር ሽብርተኝነትን ትደግፋለች፤ ከኢራን ጋርም ተወዳጅታለች የሚል ነበር።

በትናንቱ የአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ከሁለቱ ጎራ የሆኑ አገራት ዲፕሎማቶች የተወራወሯቸው ቃላት የባህረ ሰላጤው አገራት ውዝግብ ጡዘት የደረሰበትን ደረጃ ያሳየ ነው ተብሏል።

በስብሰባው የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራንን ሲያወድሱ እና ከዶሃ ጋር ፀብ ውስጥ የገቡትን የባህረ ሰላጤው አገራትን ሲወርፉ ተደምጧል።

በተቃራኒው የግብፅና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኳታር ሽብረተኞችን የመደገፍ የቆየ ታሪክ እንዳላት ሲያነሱ እና ከኢራን ጋር ለገባችው ፍቅር ዋጋ እንደምትከፍል ሲዝቱ ነበር።

ምንጭ፦ አልጀዚራ