ኩርድ ራሷን የቻለች ሀገር እንድትሆን እደግፋለው- እስራኤል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እስራኤል ኩርድ ራሷን የቻለች ሀገር እንድትሆን ድጋፏን እንደምትሰጥ አስታወቀች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ዛሬ በሰጡት አስተያየት፥ ኩርድ እንድ ሀገር እንድትቋቋም እስራኤል ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

በኢራቅ የሚገኙት ኩርዳውያን እንደ ሀገር ለመቋቋም ከሳምንት በኋላ ሊያካሂዱት ላሰቡት ህዝበ ውሳኔ የኢራቅ ምክር ቤት እውቅና መነፈጉ ተነግሯል።

ይሁን እንጂ ኔትኒያሁ ኩርዳዊያን ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ እስራኤል ድጋፏን እንደምትሰጥ ገልጸው ይህንኑ የሚያስተባብሩ አካላትን ከጽህፈት ቤታቸው እንደሚልኩም አስታውቀዋል።

እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1960 ወዲህ ከኩርዶች ጋር ሚስጥራዊ የሆነ ወታደራዊ እና የንገድ ግንኙነት እንዳላት ይነገራል።

የኩርዶች በአሁኑ ጊዜ በኢራቅ፣ ቱርክ፣ ሶሪያ እና ኢራን ውስጥ ተከፋፍለው እንደሚገኙ ይታወቃል።

በኢራቅ የሚገኙ ኩርዶች መሪ ማሶውድ ባርዛኒ በትናንትናው እለት አንደተናገሩት፥ “ምንም አንኳ የኢራቅ ፓርላማ ሀዝበ ውሳኔውን እውቅና ቢነፍገውምእኛ ግን እንዲካሄድ ጫና አንፈጥራለን” ብለዋል።

የኢራቅ ጉረቤቶች የሆኑት ቱርክ፣ ሶሪያ እና ኢራን ህዝበ ውሳኔውን መቃወማቸው የተነገረ ሲሆን፥ ምክንያቱ ደግሞ በሀገራቸው የሚገኙ የኩርድ ህዝቦች በዚህ ነገር እንዳይነሳሱ በመፍራት ነው ተብሏል።

ምንጭ፦ www.reuters.com