በደብረ ማርቆስ 2 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ለሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደብረማርቆስ ከተማ በመንግስትና በባለሀበቶች ቅንጅት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለጹት፥ መንግስት ከህዝቡና ከባለሃብቱ ጋር በመተባበር የሀገሪቱን የሕዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ በበኩላቸው፥ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ሲገቡ ሕብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ናቸው ብሏል።

ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሀገር ውስጥና በውጪ ባለሀብቶች የሚገነባው አማዞን የችፑድ ማምረቻ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ መሆኑ ነው የተነገረው።

ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው ባለ ሁለት ፎቅ ሆስፒታልና ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ዘመናዊ የመንገድ መብራት ዝርጋታም ከልማት ፕሮጀክቶቹ መካከል ተጠቃሽ ነው።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ