የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች የህዳሴውን ግድብ እየጎበኙ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ የውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስተሮች የህዳሴውን ግድብ እየጎበኙ ነው።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የሱዳኑ አቻቸው ሙአተዝ ሙሳ እና የግብጹ ውሃ ሃብትና መስኖ ሚኒስትሩ መሃመድ አብደል አቲ ናቸው በጉባ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየጎበኙ ያሉት።

የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የሶስቱ ሀገራት ሚኒስትሮች በታላቁ ህዳሴ ግድብ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሚኒስትሮቹ በአሁኑ ሰዓት በኢንጅነር ስመኘው በቀለ አስጎብኚነት የግድቡን አጠቀላይ ግንባታ እየጎበኙ ነው።

የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ከዚህ በፊት ግድቡን በተናጠል የጎበኙት ቢሆንም፥ በአንድ ላይ ግድቡን ሲጎበኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ጉብኝቱን ተከትሎም ነገ የሚኒስትሮቹ የሶስትዮሽ ስብሰባ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በስብሰባው ሚኒስትሮቹ በህዳሴው ግድብ ወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን፥ እንዲጠኑ ብሎ በሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት የሚጠኑትን ሁለት ጥናቶች በተመለከተ ውይይት ያደርጋሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለቱን ጥናቶች ለማስጠናት እና ጥናቶቹ ያሉበትን ደረጃ ለመከታተል ሶስቱ ሃገራት የሶስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እና በመካከላቸው ያለውን መተማመን ለማጎልበት በማሰብ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች።

ሁለቱ ጥናቶች የሚደረጉት በሶስቱ ሃገራት እና በአማካሪ ድርጅቶቹ መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት እና በሶስቱ ሃገራት መሪዎች መካከል በተፈረመው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት ነው።

ይህ መሆኑንም በሃገራቱ መካከል በጉዳዩ ላይ ያለው ትብብር እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።