ሳዑዲ የቀደሞ ሉዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ናይፍና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሂሳብን አገደች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ ዓረቢያ የቀደሞ ሉዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ናይፍ እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ የሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ አገደች።

ባሳለፍነው ሰኔ ወር በንጉስ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ከአልጋ ወራሽነታቸው ተነስተው በንጉሱ ልጅ ሞሃመድ ቢን ሳልማን የተተኩት ናይፍ በፀረ ሙስና ዘመቻው ትኩረት ከተደረገባቸው ንጉሳዊ ቤተሰቦች አንዱ ናቸው።

በዚህም በቀድሞው አልጋ ወራሽ ልዑል ስም የተከፈቱም ሆኑ የዘመዶቻቸው የባንክ የሂሳቦች ታግደዋል ነው የተባለው።

ሳዑዲ ይህን እርምጃ የወሰደችው በንጉስ ሳልማን የተቋቋመው እና በአልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን የሚመራው የፀረ ሙስና ግብረ ሃይል ሌሎችን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገው እንቅስቃሴ አንድ አካል በመሆኑ ነው።

የፀረ ሙስና ዘመቻው ባሳለፍነው ቅዳሜ የተጀመረ ሲሆን በርካታ ሉዑላን፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች ተይዘዋል።

የ11 ሉዑላን፣ የ4 ሚኒስትሮች እና የበርካታ የቀድሞ ሚኒስትሮች እንዲሁም የባለሃብቶች በቁጥጥር ስር መዋል የፀረ ሙስና ዘመቻው ጅማሬ ነው ብላለች ሳዑዲ።

በርካታ የሀገር ውስጥ የባንክ የሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ያገደች ሲሆን፥ ቁጥራቸውም 1 ሺህ 700 ደርሷል።

ቀድሞው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ናይፍ ከሃላፊነት ከተነሱበት ጊዜ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ የታዩት ባሳለፍነው ማክሰኞ የአሲር ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት ልዑል መንሱር ቢን ሙቅሪን ቀብር ላይ ነው።

ሟቹ ልዑል በሄሊኮፕተር አደጋ ያለፈው እሁድ መሞታቸው ይታወቃል።

 

 

 

ምንጭ፦አልጀዚራ