ሳዑዲ በፀረ ሙስና ዘመቻዋ በትንሹ 100 ቢሊየን ዶላር መመዝበሩን ደርሼበታለሁ አለች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳዑዲ ዓረቢያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሀገሪቱ 100 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በከባድ ሙስና መመዝበሩን በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።

በሶስት ዓመታት በተሰራ የምርመራ ግኝት መሰረት ገንዘቡ የተመዘበረው ባለፉት አስርት ዓመታት መሆኑን ጠቁሟል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሼክ ሳኡድ አል ሞጀብ፥ በአሁኑ ወቅት 199 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።

ምርመራ እየተደረገባቸው ከሚገኙት መካከል ባሳለፍነው ቅዳሜ በቁጥጥር ስር የዋሉት፥ ልዑላን፣ ሚኒስትሮች እና የንግድ ሰዎች ይገኙበታል ነው ያሉት።

ሼክ ሞጄብ በፀረ ሙስና ዘመቻው በተገኘው የማጣራት ስራ የመንግስት ሃብት ባልተገባ ሁኔታ መመዝበሩን የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

አሁን ባለው የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ እና የተጠርጣሪዎችን ንብረት የማገድ ስራ መደበኛ የንግድ ስርዓቱ በጤናማ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የተጠርጣሪዎች እና ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የግል የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ እየታገደ መሆኑንም ነው የገለፁት።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በልዑል አልጋ ወራሽ የሚመራው ሀገራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የመመርመር እና የመቆጣጣር ስራዎችን በፍጥነት እያከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም 208 ሰዎች ለምርመራ ተይዘው የነበረ ሲሆን፥ ሰባት ሰዎች ያለምንም ክስ በነፃ ተሰናብተዋል ነው ያሉት።

የተፈፀመው ሙስና አሁን ከተገመተው በላይ የመሆን እድል እንዳለውም ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በሳዑዲ ህግ መሰረት ሙሉ መብታቸው እንደሚከበር፣ በምርመራ እና በክስ ሂደት ግለሰባዊ መረጃዎቻቸው በሚስጥር እንደሚጠበቁላቸውና ለማንም ይፋ እንድማይደረግ ገልፀዋል።

ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል ቢሊየነሩ ልዑል አልዋሌድ ቢን ታለል እና ከብሔራዊ ዘብ ሃላፊነት የተነሱት ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ ይገኙበታል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ