አሜሪካ ፍትሃዊ ያልሆነ የንግድ ተግባርን አትታገስም- ፕሬዚዳንት ትራምፕ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በእሲያ ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በቬትናም በመካሄድ ላይ በሚገኘው በእሲያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (አፔክ) ጉባዔ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አሜሪካ ለሁሉም ፍትሃዊ ላልሆነ የንግድ አሰራር ምንም አይነት ትእግስት የላትም ሲሉ ተናግረዋል።

የእሲያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (አፔክ) ሀገራት ፍትሃዊ በሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው አሜሪካም ከእነሱ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነች ሲሉም ለጉባዔው ተሳታፊዎች አብራርተዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ፥ ነፃ የንግድ ውድድር በሚሊየን የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን ስራ አሳጥቷል፤ ይህንን ፍትሃዊ ያልሆነ ነገር ለማስተካከል እና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂምፒንግ በጉባዔው ላይ በመገኘት ንግግር ማድተጋቸውም ተነግሯል።

የእሲያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (አፔክ) በፓሲፊክ አካባቢ የሚገኙ የ21 ሀገራትን ኢኮኖሚ አንድ ላይ የሚያመጣ ሲሆን፥ ይህም የዓለማችንን 60 በመቶ ኢኮኖሚ የሚሸፍን ነው።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእሲያ ሀገራት ለ12 ቀናት የሚቆይ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፥ እስካሁንም ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይናን ጎብኝተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ከ12 የእሲያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (አፔክ) ሀገራት ጋር የንግድ ስምምነት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

ፕሬዚዳን ዶናልድ ትራምፕ የአፔክ ሀገራት ጉባዔ ላይ ተሳትፈው ካጠናቀቁ በኋላም ወደ ቬትናሟ ዋና ከተማ ሃኖይ በማቅናት በሀገሪቱ ይፋዊ ይሳራ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ12 ቀናት የእሲያ ሀገራት ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውም የፊታችን ሰኞ ህዳር 4 2010 በፊሊፒንስ በሚያደርጉት ጉብኝት ይጠናቀቃል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ