የቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ግንባታ 60 በመቶ ተጠናቋል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በ350 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት የማስፋፊያ ስራው እየተከናወነ የሚገኘው የቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማስፋፊያ ግንባታ አብዛኛው የሲቪል ስራው ተጠናቋል።

የቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሚያስተናግደው የመንገደኞች ብዛት ጋር አንጻር ተመጣጣኝ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ የዛሬ ሶስትአመት የማስፋፊያ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተካሄደ ያለው የማስፋፊያ ግንታባታ፥ ከዚህ ቀደም በክፍል ብቻ ተገድቦ የነበረውን ልዩ እንግዶች ማስተናገጃ (ቪ አይ ፒ) ህንጻ ለብቻ የሚያካትት ነው።

ህንጻው ወደ መዲናይቱ የሚመጡ ባለስልጣናትን ለማስተናገድ እና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የያዘ ነውም ተብሏል፡፡

በሶስት አመት ወስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የማስፋፊያ ግንባታ ግን በዲዛይን ክለሳ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ሳቢያ ከተባለው ጊዜ እንደሚዘገይ፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴወድሮስ ዳዊት ተናግረዋል።

አሁን ላይም የተርሚናሉ ማስፋፊያ የሲቪል ስራ ከተወሰኑ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ውጭ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ይናገራሉ፤ ግንባታውም በመቶኛ 60 በመቶ ላይ ደርሷል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም ተርሚናሉ ከዚህ ቀደም በአመት ያስተናግድ ከነበረው ከ6 እስከ 7 ሚሊየን የመንገደኞች ቁጥር ወደ 22 ሚሊየን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ማስፋፊያው ከደህንነትም ሆነ ከፍተሻ አንጻር ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር የሚያስቀርና የመንገደኞችን ፍሰት የሚያሳልጥ ሲሆን፥ የመንገደኞችን እርካታ ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም ነው አቶ ቴወድሮስ የተናገሩት።

በተለያዩ ዘርፎች ተከፍሎ እየተሰራ ያለው ይህ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታም ሰኔ ወር ላይ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ከማስፋፊያ ስራው ባለፈ ግን አየር መንገዱ እየጨመረ የመጣውን የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት ለማርካት፥ በአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ጥናት እያካሄደ መሆኑንም አቶ ቴወድሮስ ጠቁመዋል።

ለዚህም 10 ሳይቶች የተመረጡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ ተለይተው የተሻለውን ለመምረጥ ለሚመለከተው የበላይ አካል መተላለፉንም አስረድተዋል።

ምርጫው እንደ ጸደቀም የማስተር ፕላን እና ዝርዝር የቴክኒክ ስራዎች ይጀመራሉ ነው ያሉት፡፡

 

 


በሰርካለም ጌታቸው