16 ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ስያሜ ላይ ከድምዳሜ ሳይደርሱ ተለያይተዋል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) 16 ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያካሄዱ ባለው ድርድር በምርጫ ቦርድ ስያሜ ላይ ዛሬም ከድምዳሜ ሳይደርሱ ተለያይተዋል።

ፓርቲዎቹ በዋናነት የምርጫ ቦርድ አሁን የያዘውን ስያሜ ይዞ ይቀጥልና ስያሜው ኮሚሽን በሚል ይቀየር የሚል የድርድር ሀሳብ በመያዝ ነው ከድምዳሜ ያልደረሱት።

ኢህአዴግ የስያሜ ለውጥ የይዘት ለውጥ እስካላመጣ ድረስ ስያሜ ብቻ በመቀየር የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ለውጥ አይፈጥርም ብሏል።

ከስያሜው ባሻገር በይዘቶች፣ በአቅም ክፍተት፣ የቦርዱ ስልጣንና ተግባር ላይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ካሉ፥ በድርድር ሂደቱ በውይይት መመልከት እንደሚቻል የኢህአዴግ ተደራዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተናግረዋል።

መኦዴፓ፣ መኢብን፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲና ኢራፓ፥ በስያሜው ላይ ቀድመው የያዙትን አቋም በመቀየር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስያሜ ባለበት ቢቀጥል እንደሚስማሙ ገልፀዋል።

የ11 ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ደግሞ ስያሜው ወደ ምርጫ ኮሚሽን እንዲቀየር እና 15 አባላት ያሉትና የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላትን የሚያካትት ቦርድ እንዲዋቀር የሚል ሀሳብ አቅርቧል።

ቦርዱ የፖሊሲ ጉዳዮችን ብቻ እንዲመለከትና ኮሚሽኑ ደግሞ በመደበኛነት የምርጫ ስራና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲያከናውን በማለት ሀሳቡን ገልጿል።

ኢህአዴግ ከፓርቲዎቹ በቀረበው የድርድር ሀሳብ የምርጫ ቦርድ ስያሜን ሊያስቀይር የሚችል ምክንያት አልቀረበም ነው ያለው።

በመሆኑም ያለበቂ ምክንያት ህገ መንግስት ላይ የሰፈረን ስያሜ መቀየር አግባብ አይደለም ሲል የመጨረሻ አቋሙን አሳውቋል።

በምርጫ ቦርድ ስያሜ ላይ ፓርቲዎቹ ከድምዳሜ ባለመድረሳቸው ለቀጣይ ሳምንት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዘዋል።

 

በበላይ ተስፋዬ