ኢትዮጵያ ለሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠ/ሚ ሃይለማርያም ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፍትሃዊና ሠላማዊ እንዲሆን ድጋፏን እንደምትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰናባቹን የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት አህመድ ሙሃመድ ማህሙድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች ሶማሌ ላንድ በመጪው ሰኞ በምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያም መክረዋል።

ከዚህ ባለፈም ምርጫው ህዝቡ በንቃት የሚሳተፍበት፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም ተቀባይነት እንዲኖረው በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።

ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የበኩሏን ሚና እንደምትጫወት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፋጠንም የጋራ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በትኩረት ለመሥራት ተስማምተዋል።

የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያና ሶማሌ በጸጥታ፣ በንግድ፣ በትምህርት፣ በግብርናና ሌሎች መስኮች ያላቸው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አንስተዋል።

ምርጫው ሠላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

ሶማሌ ላንድ ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም አራተኛውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።