ሀገር ውስጥ ከገባው 12 ሚሊዮን ኮንዶም 9 ሺው ጥራቱን ያልጠበቀ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከአንድ ወር በፊት ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው 12 ሚሊዮን ኮንዶም 9 ሺህ ኮንዶም ጥራቱን ያልጠበቀ ሆኖ መገኘቱን የመድሀኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ አሳወቀ።

ኤጀንሲው እንዳለው ዶንክ ቡክ ከተሰኘው የቬትናም ኩባንያ ከተገዛው ኮንዶም ጥራቱን ያልጠበቀው እንዲመለስ እየተደረገ ነው።

አቅራቢው ድርጅት በገባው ውል መሰረትም ኮንዶሙን መተካት ወይም ገንዘቡን የሚመልስ መሆኑን ነው የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብርሀም ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ኮንዶሞች የሚገዙት የአለም ጤና ድርጅት እውቅና ከሰጣቸው ኩባንያዎች መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ሎኮ፥ ኮንዶሞቹ ወደ ሀገር ውስጥ ሳይገቡም ጥራታቸው የሚረጋገጥ ቢሆንም ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላም ከመሰራጨታቸው በፊት ጥራታቸውን በድጋሚ የማረጋገጥ ስራ ይሰራል።

ድጋሚ የማረጋገጥ ስራ ሲሰራ ጥራቱን ያላሟላ ኮንዶም የሚመለስ መሆኑ ተገልጿል።

ኤጀንሲው በዚህ ዓመትም ከ400 ሚሊዮን በላይ ኮንዶሞችን እንደሚያስገባ ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል።

 

 

በዙፋን ካሳሁን