የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለ8 ሺህ ታጋዮች እውቅና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለ8 ሺህ ታጋዮች እውቅና ሊሰጥ ነው፡፡

የድርጅቱን የምስረታ በዓል ''የብአዴን ህዝባዊነት እና የዓላማ ፅናት ለዴሞክራሲያዊ አንድነት'' በሚል መሪ ቃል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮነን፥ ''ብአዴን ባለፉት 37 ዓመታት ህዝባዊ ዓላማ አንግቦ ፈታኝ ሁኔታዎችን በፅናት እየታገለ በድል የተጓዘ ድርጅት ነው'' ብለዋል።

ለተመዘገበው ስኬት በትግሉ ወቅትም ሆነ ከትግል በኋላ በልማት እና መልካም አስተዳደር መስፈን አኩሪ ተጋድሎ ለፈፀሙ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት መታሰቡን ገልፀዋል።

የእውቅና አሰጣጡ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም የዞን ማዕከላት በሚካሄዱ ኘሮግራሞች እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

እውቅና አሰጣጡም ታጋዮች ለህዝብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በህዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ከማድረጉም ባለፈ ለአዳዲስ ታጋዮች ደግሞ ብርታት መስጠት ዓላማ ያደረገ ነው።

የእውቅና አሰጣጡ ለሦስተኛ ዙር የሚሰጥ ሲሆን፥ ቀደም ሲል መስራች ታጋዮችን እና ሌሎች ታጋዮችን በመለየት እውቅና ተሰጥቷል።

በዓሉን በተለያዩ የልማት ስራዎች፣ በከተማ ፅዳት እና ውበት እንዲሁም በሌሎች ፕሮግራሞች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ አለምነው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በበዓሉ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው ግለቱን ጠብቆ በሚቀጥልበት ጉዳይ ላይ አብይ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

''በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በተለይ ለድርጅቱ አመራር እና አባላት የታጋይነት እና የለውጥ ሃሳብ መሪነት እንዲሁም ታግሎ የማታገል መንፈስ በሚያዳብር ሁኔታ ይከበራል'' ብለዋል።

በከተማ እና በገጠር እየተመዘገቡ የሚገኙ ሁለንተናዊ ለውጦችን እና ስኬቶችን ተገንዝቦ በተደራጀ የለውጥ ንቅናቄ ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታም ዓመታዊ በዓሉ ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን በሚፃረር ዙሪያ እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመመከት እና በማምከን ለሃገራዊ አንድነት በጋራ መቆም በሚያስችሉ አጀንዳዎች በሰፊው እንደሚመክርም አብራርተዋል።

''ብአዴን የቀደመ የዓላማ ፅናቱን እንደተላበሰና ህዝባዊነቱን እንዳነገበ የሚቀጥል ድርጅት'' ነው ያሉት አቶ አለምነው በልማት ስራዎች የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመለየት የመጎብኘት እና ምርጥ ተሞክሮዎችን የመቀመር ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

የህዝቡን እና የድርጀቱን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት አጠናክረው በሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

ብአዴን የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች፣ ወጣቱ፣ ህዝቡ ከድርጅቱ ጎን ተሰልፎ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል።

የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ እንዲያብብ በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም ብአዴን ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ