ትራምፕና ፑቲን አይ ኤስን ከሶሪያ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን አይ ኤስን ከሶሪያ ሙሉ በሙሉ  ለማስወገድ ተስማሙ።

ክሬምሊን ባወጣው መግለጫ ሁለቱ መሪዎች ከእስያ ፓስፊክ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን፥ በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል ነው ያለው።

ከዋሽንግተን በኩል ስለመግለጫው ይፋዊ ማረጋገጫ እስካሁን አልወጣም።

ትራምፕ እና ፑቲን በስምምነታቸው በሶሪያ ሰላምን ለማስፈን ወታደራዊ አማራጭ መፍትሄ አይሆንም ብለዋል።

ከወታደራዊ አማራጭ ይልቅ በሶሪያ አይኤስን ለማውገድ የሚመለከታቸውን ተቃዋሚ ሃይሎች ያሳተፈ የሰላም ድርድር በጀኔቫ መካሄድ አለበት የሚል ነው።

ሩሲያ ባለፉት ስድስት ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት የሶሪያ መሪ የበሽር አል አሳድ መንግስት አጋር በመሆን ዘልቃለች።

አሜሪካ በአንፃሩ የሶሪያ አረብ እና የኩርድ ሃይሎችን በመደገፍ ከ2014 ጀምሮ የአየር ሃይል ጥምር ጥቃት እና የምድር ጦር ከአይ ኤስ ጋር ውጊያ ስታደርግ ቆይታለች።

አይ ኤስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶሪያ ቁልፈ ይዞታዎችን እየተነጠቀ ነው።

ባለፈው ወር በአሜሪካ የሚደገፉት የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ራቃ ከተማን ሙሉ በመሉ መቆጣጠራቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ እና የቭላድሚር ፑቲን ግንኙነት የሚጠበቅ ቢሆንም ዝርዝር መረጃዎች ግን አልወጡም።

ጉባኤው እየተካሄደ በሚገኝባት የቬትናም የወደብ ከተማ ዳ ናንግ ከዓርብ ጀምሮ አብረው ናቸው።

ሁለቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው የመከሩት ባሳለፍነው ሃምሌ ከቡድን 20 ሀገራት ስብስባ ጎን ለጎን በጀርመኗ ከተማ ሃምቡርግ ነበር።

ትራምፕ ከሞስኮ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ነው።

በተለይም በ2016 የአሜሪካ ምርጫ ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች የሚለው ውንጀላ ፕሬዚዳንቱን በአሜሪካ ፖለቲከኞች በትኩረት እንዲታዩ አድርጓቸዋል።

ዋሽንግተን መርማሪ ቡድን አቋቁማ ጉዳዩን በጥልቀት እያጣራች ሲሆን፥ የትራምፕ የቀድሞ አማካሪዎችና ረዳቶችም ተከሰዋል።

ክሬምሊን እና ትራምፕ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብነት የሚሰነዘርባቸውን ውንጀላ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።


ምንጭ፦ቢቢሲ