ከአየር ጤና አደባባይ እስከ ጊቤ ወንዝ ያለው መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከአዲስ አበባ አየር ጤና አደባባይ እስከ ጊቤ ወንዝ ድረስ ያለው መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት ይጀመራል ተባለ።

ከ175 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ ግንባታ የኢትዮጵያ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች እንደሚያከናውኑትም ታውቋል።

ከመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሚያከናውነው 172 ኪሎ ሜትሩን ሲሆን፥ ቀሪውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ነው የሚገነባው።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የዲዛይን ዳይሬክተር ኢንጅነር ሰመረ ጅላሉ፥ ከአየር ጤና አደባባይ እስከ ወለቴ ኖክ ያለው መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት ግንባታቸው ይጀመራሉ ተብለው እቅድ ከያዛቸው መንገዶች አንዱ ነው ብለዋል።

የመንገዱ የዲዛይን ስራም ከ2 ወር በኋላ እንደሚጠናቀቅ ኢንጂነር ሰመረ አስታውቀዋል።

በባለስልጣኑ የሚገነባው መንገድ ከ3 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሲሆን፥ ለመንገዱ ግንባታ ለዚህ ዓመት ብቻ 40 ሚሊየን ብር በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን በጀት ተይዞለታልም ብለዋል።

አሁን እየተሰራለት ያለው ዲዛይን የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ከ30 ሜትር በላይ ስፋት ያለው እና ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጥ መሆኑን ነው ኢንጅነር ሰመረ የሚናገሩት።

የኢትየጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ከኖክ አደባባይ እስከ ጊቤ ወንዝ ያለውን መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት ለማስጀመር እቅድ መያዙን አስታውቋል።

በባለስልጣኑ የአለም ገና መንገድ ኔትዎርክ ዳይሬክተር ኢንጅነር ሳምሶን ተስፋዬ፥ ባለስልጣኑ የመንገዱን ዲዛይን ስራ ማጠናቀቁን እና በጥር ወር ግንባታውን እንደሚያስጀምር ገልፀዋል።

መንገዱ አሁን ካላይ 7 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፥ አዲስ በሚገነባበት ጊዜ ግን የእግረኛ መንገድን መንገድን ጨምሮ 22 ሜትር ስፋት ይኖረዋልም ብለዋል።

ለመንገዱ ግንባታ ለዚህ ዓመት ብቻ ከ250 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት የሚሸፈን በጀት ተይዞለታል።

ከአየር ጤና አደባባይ እስከ ጊቤ ወንዝ ያለው እና በሁለቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ግንባታው የሚከናወነው መንገድ እስከ 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የመንገዱን ግንባታ ጥራት እና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም በሁለቱም መስሪያ ቤቶች ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት አሰራር ዘርግቷል።

ከኖክ አደባባይ እስከ ጊቤ ወንዝ ያለው መንገድ 172 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፥ አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ቡታጅራ፣ ሆሳዕና እና ሌሎች ከተሞች የሚያገናኝ መስመር ነው።

 

በዙፋን ካሳሁን