ደቡብ ሱዳን የምግብ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የቀረበባትን ውንጀላ አጣጣለች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ደቡብ ሱዳን የምግብ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የቀረበባትን ውንጀላ አጣጥላለች።

ሀገሪቱ በሰሜናዊ የወው እና የባህረ ኤል ጋዛል ክልሎች ሆን ብላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲራቡ በማድረግ ምግብን እንደጦር መሳሪያ ተጠቅማበታለች የሚለው ውንጀላ ሀሰት ነው የሚል ማስተባበያ ሰጥታለች።

የፕሬዚዳንት ኪር ቃል አቀባይ አቴኒ ዌክ አቴኒ እንደተናገሩት፥ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የደቡብ ሱዳን የማዕቀብ ኮሚቴ የደረሰው ሪፖርት መሰረተ ቢስ ነው።

የሀገሪቱ መንግስት በክልሎቹ ሰብዓዊ ድጋፎች በፍጥነት እንዲደርሱ እያደረገ ያለውን ጥረት ከግምት ያላስገባ ሪፖርት መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።

የደቡብ ሱዳንን ህዝቦች መንግስት ሊያስተዳድራቸው የሚፈልግ በመሆኑ ሆን ተብሎ የሚቀርብላቸውን ምግብ በማቋረጥ እንዲራቡ አልተደረገም ነው ያሉት።

በቅርቡ የወጣው የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት በወው አካባቢ የሚደርሱ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በመከልከል በርካታ ሰዎች ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡና በርሃብ ምክንያት እንዲሞቱ ተደርጓል የሚል ነው።

ሆኖም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ባሳለፍነው ሳምንት የፀጥታ ሃይሎች በግጭት አካባቢዎች የሚደርሱ ሰበዓዊ እርዳታዎችን እንዳያስተጓጉሉ አዘዋል።

በዚህም ርሃብ ለተጋረጠባቸው የግጭት አካባቢዎች የምግብ እርዳታዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ ፈቅደዋል።

http://www.plenglish.com